በፓኪስታን እስልምና ላይ ተሳልቀዋል በሚል የተከሰሱ አራት ሰዎች የሞት ፍርድ ተላለፈባቸው
ሀገሪቱ ከ1980 ጀምሮ እስልምናን የሚጎዱ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ በሚል ይህን ቅጣት ትጥላለች
የግለሰቦቹ ጠበቃ ግን በደንበኞቹ ላይ የተላለፈው ፍርድ የተጋነነ ነው በሚል ይግባኝ እጠይቃለሁ ብሏል
በፓኪስታን እስልምና ላይ ተሳልቀዋል በሚል የተከሰሱ አራት ሰዎች የሞት ፍርድ ተላለፈባቸው።
በእስያዊቷ ፓኪስታን ቅዱስ ቁርዓንን ጨምሮ የእስልምናን ዕምነት እሴቶችን ጎድተዋል በሚል በአራት ተከሳሾች ላይ የሞት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ተከሳሾቹ የእስልምና እምነትን የሚያንቋሽሹ ይዘቶችን በማህበራዊ የትስስር ገጾች አሰራጭተዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው ክርክሩ ሲካሄድ ቆይቷል።
ከሰሞኑ በራዋልፒንዲ ከተማ በተካሄደ ችሎት ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል በሚል አራቱም ተከሳሾች የሞት ፍርድ ተላልፎባቸዋል ተብሏል።
ግለሰቦቹ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች እሴቶችን፣ ቅዱስ ቁርዓንን፣ እምነትን እና ሌሎች ተያያዥ እሴቶችን አንቋሸዋል ሲል አል አረቢያ ዘግቧል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ላይ ከሞት ፍርድ በተጨማሪ 16 ሺህ 500 ዶላር እንዲከፍሉም ቅጣት ተላልፎባቸዋል ተብሏል።
የተከሳሾቹ ጠበቃ በበኩሉ በደንበኞቹ ላይ የተላለፈው ፍርድ ተመጣጣኝ አይደለም በሚል ተቃውሟል።
በደንበኞቹ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ለማስቀየር ይግባኝ ለማለት በዝግጅት ላይ እንደሆነም ጠበቃቸው ተናግሯል።
የፍርድ ቤቱ ዳኞች በተከሳሾቹ ላይ የሞት ፍርድ ብለው ያስተላለፉት የደቦ ፍርድ እንዳይፈጸምባቸው ፈርተው ያስተላለፉት ሊሆን እንደሚችልም ጠበቃው አክሏል።
ፓኪስታን በእስልምና ዕምነት እና እሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለማስቀረት ከ1980 ጀምሮ ህግ አዘጋጅታለች።
በፓኪስታን ዕምነቱን የሚያንቋሽሹ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ይህ የመጀመሪያው ሳይሆን ከዚህ በፊት እስልምናን አንቋሸዋል በሚል በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና በደቦ ፍርድ የተገደሉ ዜጎች እንዳሉም ተገልጿል።