ዲፕሎማቶቹ ፓኪስታን ሩሲያን እንድታወግዝ በፊርማ ጠይቀዋል
የ22 ሀገራት ትልልቅ ዲፕሎማቶች በጋራ በመሆን የፓኪስታን መንግስት ተመድ በሩሲያ ላይ ያዘጋጀውን የውሳኔ ሃሳብ እንዲደግፍ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ።
ጥያቄውን በጋራ ካቀረቡት መካከል የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት እንደሚገኙበትም ተገልጿል። የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ሩሲያ “በዩክሬን ወረራ” እንደፈጸመች ተደርጎ የቀረበ ሲሆን፤ ኢስላማባድ ይህን እንድትደግፍ ጥያቄ ቀርቦላታል።
ፓኪስታን፤ የሩሲያን ድርጊት እንድታወግዝ ሀገራቱ ጥያቄያቸውን በፊርማ አቅርበዋል። የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት ሆነው ፓኪስታን ሩሲያን እንዲታወግዝ በፊርማ የጠየቁት ኦስትሪያ፣ ቤልጀም፣ ቡልጋሪያ፣ቼክ ሪፐብሊክ፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ ሃንጋሪ፣ ጣሊያን፣ ፖርቹጋል፣ ፖላንድ፣ ሮማኒያ፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ እና ኔዘርላንድስ ናቸው።
ከዚህ ባለፈም አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ፣ ስዊዘርላንድና ብሪታኒም ኢስላማባድ፣ ሞስኮን እንዲታወግዝ በፊርማቸው የጠየቁ ናቸው።
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሞስኮ ከመሄዳቸው አስቀድሞ የዩክሬን ቀውስ ከሀገራቸው ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር እንደሌለ የገለጹ ሲሆን፤ ኢስላማባድ የትኛውንም ወገን መቀላቀል እንደማትፈልግ አስታውቀዋል።
ባለፈው ሳምንት የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ሞስኮ እንደነበሩ ተዘግቧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቭላድሚር ፑቲንን ያገኙት ጦርነቱ ከተጀመረ ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑ ተገልጿል።
ፓኪስታን የተጀመረው ጦርነት እንዳይከሰት ማድረግ አለመቻሉ “ጸጸት” ውስጥ እንደከተታት አስታውቃለች።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ወታደራዊ ተልዕኮ እንዲፈጸም ትዕዛዝ በሰጡ በሰባተኛው ቀን ጦራቸው በደቡብ ዩክሬን የምትገኘውን ኬርሰንን መቆጣጠሩ ተገልጿል።
የሰላም ንግግር የጀመሩት ዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ባያቆሙም ለዳግም ንግግር ተቀጣጥረዋል።