የፓኪስታኑ ጠ/ ሚኒስትር፣ አሜሪካ በሩሲያ ባደረጉት ጉብኝት ደስተኛ አለመሆኗን ገለጹ
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የመተማመኛ ድምጽ የውሳኔ ሃሳብ አዘጋጅተዋል
ለፓኪስታን ጠ/ሚኒስትር የሚሆን ሰው ከ342 የም/ቤት አባላት ውስጥ ይመረጣል
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን በሩሲያ አድርገውት የነበረው ጉብኝት ለአሜሪካ ምቾት እንዳልሰጣት አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሩሲያ በመሄዳቸው አሜሪካ ደስተኛ እንዳልሆነች ገልጸዋል፡፡አሜሪካ በፓኪታን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደገባች እስላማባድ ያስታወቀች ሲሆን ይህንን ተቃውሞዋን በይፋ ገልጻለች፡፡ በዚህም መሰረት የፓኪስታን መንግስት በእስላማባድ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ “ዋሸንግተን በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው” የሚል ተቃውሞ ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልዕክታቸው በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ያለችው አሜሪካ ነች ካሉ በኋላ አስተካክለው አንድ ምዕራባዊ ሀገር ነች ማለታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡ ኢምራን ካሃን ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እንዲነሱ የተቀነባበረ ሴራ እየተሰራባቸው መሆኑን የገለጹ ሲሆን ይህንንም በይፋ እየገለጹ ነው፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የተነሳውን “ጣልቃ ገብታችኋል” አስተያየት አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ እንደሌለም ተጠቅሷል፡፡
የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት መጋቢት 28 ቀን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የመተማመኛ ድምጽን የተመለከተ የውሳኔ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ አንድ የውጭ ሀገር “ሴራ እያደረገባቸው” እንደሆነ የሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው በሀገሪቱ የዋጋ ንረት እንዲከሰትና የአስተዳደር እጦት እንዲመጣ አድርጓል በሚል ትችት ይቀርብበታል፡፡
በቀረበው የመተማመኛ ድምጽ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ዛሬ ድምጽ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሀገሪቱ ሕገ መንግስት መሰረት 342 አባላት ካሉት ምክር ቤት አብላጫ ድምጽ ያገኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል፡፡