ፓኪስታን፤ በጎርፍ የተጎዱትን መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት 10 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል አለች
በፓኪስታን የጋጠመው የጎርፍ አደጋ ከ33 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት እንዳስከተለ መረጃዎች ይጠቁማሉ
ቻይና በጎርፉ ምክንያት ለተፈናቀሉ ፓኪስታናውያን ድጋፍ ካደረጉ ሀገራት ቀዳሚ ናት
ቻይና በጎርፉ ምክንያት ለተፈናቀሉ ፓኪስታናውያን ድጋፍ ካደረጉ ሀገራት ቀዳሚ ናት
ፓኪስታን በጎርፍ አደጋ የተጎዱትን መሰረተ ልማቶችን ለመጠገን እና መልሶ ለመገንባት ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልጋት የሀገሪቱ የፕላን ሚኒስትር አህሳን ኢቅባል ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ፤ በተለይ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በመንገድ፣ በግብርና እና ለኑሮ ወሳኝ በሆኑ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል ሲሉ መናገራቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በፓኪስታን ከሰኔ ወር ጀምሮ የዘነበው ያልተጠበቀው ክረምት ዝናብ 33 ሚሊዮን በሚሆኑት የሀገሪቱ ህዝቦች ከባድ ጉዳት እንዳስከተለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
እስካሁን በጎርፍ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 1ሺ33 መድረሱን የሀገሪቱ ብሔራዊ የአደጋ መከላከል ባለስልጣን ገልጿል።
ከባድ በሆነው የክረምት ዝናብ ምክንያት የፓኪስታን አንድ ሶስተኛው መሬት በውሃ መሸፈኑንም ነው መረጃወች የሚጠቁሙት፡፡
በተለይም በሀገሪቱ ደቡብ ምስራቅ ክልል ውስጥ የምትገኝ የሲንዲ ግዛት ያጋጠመው የጎርፍ መጥለቅለቅ በፈረንጆቹ በ2010 ከነበረው የከፋ መሆኑን ተገልጿል።
በፈረንጆቹ በ2010 በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 1 ሺህ 700 ፓኪስታናውያን የገደለ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሲንዲ ግዛት ነዋሪዎች እንደነበሩ አይዘነጋም።
አሁን ላይ ከፍተኛ መጠን ባለው ጎርፍ አደጋ የተጎዳችው ፓኪስታን ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንደምትሻ እየተነገረ ነው።
አስካሁን ባለው መረጃ፤ ቻይና በጎርፉ ምክንያት ለተፈናቀሉ ፓኪስታናውያን የሚያገለግሉ 25 ሺህ ድንኳኖችን እና የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ ዕርዳታ አንደላከች ታውቋል፡፡