ቱርክ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት የደህንነት ባለሙያዎቻቸውን ወደ ዶሃ የላኩ ሀገራት ናቸው
ፓኪስታን ለኳታሩ የአለም ዋንጫ ወታደሮቿን ወደ ዶሀ ልትልክ ነው።
በየአራት ዓመቱ አንዴ የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ በኳታር አዘጋጅነት የፊችን ህዳር ወር ላይ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡
የሩቅ ምስራቋ ፓኪስታን ደግሞ በዚህ ውድድር ላይ ጥበቃ የሚያደርጉ ወታደሮቿን ወደ ዶሃ ልትልክ መሆኗን የፓኪስታን ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ፓኪስታን ለ2022 የዓለም ዋንጫ ጥበቃ ወታደሮቿን መላክ የሚያስችላትን ህግ የሀገሪቱ ካቢኔ መወሰኑ እና ለዚህም ህግ ማዘጋጀቷ ተገልጿል፡፡
የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሻቤዝ ሸሪፍ ኳታርን በመጎብኘት ላይ ሲሆኑ ወታደሮቿን ወደ ኳታር መላክ የሚያስችላት ህግ የተዘጋጀው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡
የፓኪስታን የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ማሪዩም አውራንብ ለሮይተርስ እንዳሉት ፓኪስታን ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ጥበቃ ስራ ወታደሮቿን ለመላክ በሂደት ላይ መሆኗን ተናግረው ሁለቱ ሀገራት መቼ ስምምነቱን እንደተፈራረሙ ወይም ለመፈራረም እንዳቀዱ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
ኳታር ለፓኪስታን የሰላምና ደህንነት ድጋፍ እንዲደረግላት በይፋ ጥያቄ ማቅረቧን በረቂቅ ህጉ ላይ መመልከቱን የገለጸው የሮይተርስ ዘገባ ጥያቄውን መነሻ በማድረግም ፓኪስታን ወታደሮቿን ወደ ዶሃ ለመላክ በሂደት ላይ መሆኗ ተጠቅሷል፡፡
ኳታር እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ በይፋ ያለችው ነገር ባይኖርም ከዚህ በፊት የቱርክ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ሌሎችም ሀገራት የደህንነት ባለሙያዎቻቸውን ወደ ዶሃ እንደሚልኩ ተናግረዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት ቱርክ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር አንካራ 3 ሺህ 250 የጸጥታ ባለሙያዎች ወደ ኳታር እንደሚላኩ የተናገሩ ሲሆን ደቡብ ኮሪያ ደግሞ አምስት የቴክኖሎጂ ደህንነት ባለሙያዎችን ወደ ዶሃ መላኳ ተገልጿል፡፡