የኳታር ኢሚር ሀዘናቸው ለመግለጽ አቡዳቢ ገብተዋል
የመንግስታትና የሀገራት መሪዎች ዛሬም ወደ አቡዳቢ እንደሚገቡ ይጠበቃል
የበርካታ ሀገራት መሪዎች ኤምሬትስ ገብተዋል
የኳታሩ ኢሚር ታሚም ቢን ሃመድ አል ታኒ ከሰሞኑ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የቀድሞ የኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሀዘንን ለመካፈል አቡዳቢ መግባታቸው ተገለጸ፡፡
የኳታሩ መሪ ወደ አቡዳቢ ያቀኑት የሀገራት መሪዎች ወደ ኤምሬትስ እየሄዱ ባለበት ወቅት ነው፡፡ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ወደ አቡዳቢ ያቀኑት ሀዘናቸውን ለኤምሬትስ መሪ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አልናህያንና ለቤተሰባቸው ለመግለጽ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በኳታሩ ኢሚር ታሚም ቢን ሃመድ አል ታኒ የተመራው ልዑክ ወደ አቡዳቢ የገባ ሲሆን የቀድሞው ፕሬዝዳንትን ህልፈት ተከትሎም መጽናናትን ተመኝቷል፡፡ ኳታርና የገልፍ ሀገራት እሰጥ አገባ ውስጥ ከገቡና ማዕቀብ ከጣሉባት በኋላ የኳታርና የኤምሬትስ መሪዎች በአካል ሲገናኙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው ነው፡፡
የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ኸሊፋ ቢን ዛይድን ህልፈት ተከትሎ እስካሁን የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ፣የቱኒዝያው ፕሬዝዳንት ካይስ ሰዒድ፣ የሱዳን ወታደራዊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት ፕሬዝዳንት ጀነራል አልቡርሃን እና የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ አቡዳቢ ደርሰዋል።
በቀጣይም የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ፣ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን፣ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን፣ የፍልስጤም ራስ ገዝ ፕሬዝዳንት መሀሙድ አባስ፣ የሞሪታኒያ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ኦሉድ ሼክአል ጋዝዋኒ አቡዳቢ እንደሚደርሱ ይጠበቃል።
የዓለም ሀገራት መሪዎች ወደ አቡዳቢ እያቀኑ ያሉት ሀዘናቸውን ከመግለጽ ባለፈ ከአዲሱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነትን ለመፍጠር ነው ተብሏል።