ፖለቲካ
ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ በኋላ የመጀመሪያው የመንገደኞች አውሮፕላን ካቡል ደረሰ
PIA ወደ ካቡል ሳምንታዊ በረራዎችን እንደሚያደርግ አስታውቋል
አውሮፕላኑ የፓኪስታን ነው ተብሏል
ታሊባን አፍጋኒስታንን ከተቆጣጠረ በኋላ የመጀመሪያው የመንገደኞች አውሮፕላን በሃገሪቱ ዋና ከተማ ካቡል ደረሰ፡፡
አውሮፕላኑ ከእስላማባድ የተነሳ ሲሆን ንብረትነቱ የፓኪስታን አየር መንገድ ነው ተብሏል፡፡
‘ፓኪስታን ኢንተርናሽናል ኤር ላይንስ’ (PIA) ጥቂት መንገደኞችን አሳፍሮ ነው፤ በጦርነቱ ክፉኛ ከተጎዳው ካቡል አየር ማረፊያ የደረሰው፡፡
ይህም ወደ አፍጋኒታን የሚደረጉ የዓለም አቀፍ በረራዎች ጅማሮ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
PIA ወደ ካቡል ሳምንታዊ በረራዎችን እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ሆኖም በሳምንት ለምን ያህል ቀናት ይበራል ስለሚለው በግልጽ ያስታወቀው ነገር የለም፡፡
የሃገር ውስጥ በረራዎች በተጀመሩባት አፍጋኒስታን የኳታር አየር መንገድ ጭምር ከሰሞኑ አገልግሎትን ሲሰጥ እንደነበር ይታወሳል፡፡
እንደ ፍራንስ 24 ዘገባ ከሆነ የአሜሪካ ወታደሮች አፍጋኒስታንን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ ተቀምጦ በነበረው ቀነ ገደብ ከ120 ሺ የሚልቁ ሰዎች ከአፍጋኒስታን ወጥተዋል፡፡