ደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ ተጨማሪ እርምጃ እንዲወስድ ጠየቀች
ደቡብ አፍሪካ በጋዛ እየተከሰተ ያለው ረሃብ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም ብላለች
በጋዛ ከረሃብ ጋር በተያያዘ እስካሁን የ20 ሰዎች ህይወት ማለፉ ሪፖርቶች ያመለክታሉ
ደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በጋዛ እያደረገች ባለው ጦርነት ላይ ተጨማሪ ትእዛዞችን እና ውሳኔዎችን እንዲያሳለፍ ጠይቃለች።
ደቡብ አፍሪካ ለፍርድ ቤቱ ባስገባችው ማመልከቻ፤ በጋዛ ውስጥ የሚገኙ ፍልስጤማውያን ከረሃብ ጋር እየተጋፈጡ መሆናቸውን በማሳሰብ፤ ሁሉም ወገኖች ግጭት እንዲያቆሙ እንዲሁም ታጋቾች እና እስረኞች እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እንዲያስተላለፍ ጠይቃለች።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳት ጽህፈት ቤት ትናንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ የፍሊስጤም ህዝብ ከዚህ በላይ መቆየት አይችልም ሲል አስጠንቅቋል።
“የፍሊስጤም ህዝብ ለከፋ የረሃብ አደጋ ተጋልጧል” ያለችው ደቡብ አፍሪካ፤ ፍርድ ቤቱ “ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በፍጥነት ለማስቆም አሁኑኑ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል” በማለትም አሳስባለች።
- አለምአቀፉ ፍ/ቤት ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በተመለከተ ባቀረበችው ጥያቄ ላይ ውሳኔ አሳለፈ
- ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ምን ይዟል?
የአለም ፍርድ ቤት በመባል የሚታወቀው አይሲጄ እነዚህን እርምጃዎች መውሰድ ያለበት "በሁኔታው በጣም አጣዳፊነት" ምክንያት አዲስ ዙር ችሎቶችን ሳያዘጋጅ በቀጥታ መሆን እንዳለበትም ደቡብ አፍሪካ ጠይቃለች።
እስራኤል በጋዛ እያደረገችውን ያለውን ጦርነት ተከትሎ ከምግብ እጥረት እና ከረሃብ ጋር በተያያዘ እስካሁን የ20 ሰዎች ህይወት ማለፉ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
አምስት ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት በጋዛ የሞቱ ፍሊስጤማውን ቁጥርም ከ30 ሺህ መሻገሩን ነው የተገለጸው።
እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለውን እርምጃ በቀዳሚነት ከተቃወሙ ሀገራት አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ከዚህ ቀደም “እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍሊስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው” በማት ሀገሪቱንም በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት መክሰሷ ይታወሳል።
በሀገራት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚያስተናግደው ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ታጣቂዎች ጋር ጦርነት በምታደርግበት ወቅት የዘር ማጥፋት ድርጊቶችን ለመከላከል እርምጃ እንድትወስድ ብይን መስጠቱም ይታወሳል።
ደቡብ አፍሪካ የእስራኤል ፍሊስጤምን ጉዳይ ወደ ዓለም የወንጀል ፍርድ ቤት ይዛ ያቀናች ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያን ኔታንያሁ ላይ የእሰር ማዘዣ እንዲያወጣ መጠየቋም አይዘነጋም።