የአለም ምግብ ፕሮግራም እስራኤል በጋዛ እርዳታ እንዳላቀርብ ከልክላኛለች አለ
ድርጅቱ ከሁለት ሳምንት በፊት ያቋረጠውን ድጋፍ ለማቅረብ ምግብ የጫኑ 14 ተሽከርካሪዎች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ቢልክም እንዳይገባ መከልከሉን ነው ያስታወቀው
የአለም ጤና ድርጅት በሰሜናዊ ጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ መሆኑን ባሳወቀ ማግስት ነው የአለም ምግብ ፕሮግራም እስራኤልን የወቀሰው
የአለም ምግብ ፕሮግራም ከሁለት ሳምንታት በኋላ ወደ ሰሜናዊ ጋዛ እርዳታ ለማስገባት ያደረገው ጥረት በእስራኤል ክልከላ አለመሳካቱን አስታወቀ።
ድርጅቱ ምግብ የጫኑ 14 ተሽከርካሪዎች ወደ ሰሜናዊ ጋዛ ቢልክም የእስራኤል ጦር ድጋፉ እንዳይገባ መከልከሉን ነው የገለጸው።
ተሽከርካሪዎቹ በዋዲ ጋዛ የፍተሻ ጣቢያ ለሶስት ስአታት ከቆዩ በኋላ እንዲመለሱ መደረጉን የጠቆመው የአለም ምግብ ፕሮግራም በርካታ ሰዎች ተሽከርካሪዎቹን አስቁመው ከ200 ቶን በላይ ምግብ መዝረፋቸውን ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ድርጅቱ በጋዛ “ስርአት አልበኝነት” እየነገሰ መሆኑንና እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸመው ዝርፊያ ተበራክቷል በሚል ነበር ከሁለት ሳምንት በፊት የእርዳታ አቅርቦቱን ያቋረጠው።
እስራኤል በአለም ምግብ ፕሮግራም ለቀረበው ወቀሳ ምንም ምላሽ ባትሰጥም በጋዛ በምድርም ሆነ በሰማይ ድጋፍ እንዲደርስ እያመቻቸሁ ነው የሚሉ መግለጫዎችን ስትሰጥ ቆይታለች።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እስራኤል ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ የምትከለክልበት ምንም አይነት ምክንያት የላትም በሚል ድርጊቱን ተቃውመውታል።
ብሪታንያም የአለም ጤና ድርጅት በሰሜናዊ ጋዛ ህጻናት በረሃብ እየሞቱ ነው ባለ ማግስት ከአለም ምግብ ፕሮግራም የቀረበው ወቀሳ ያሳስበኛል ብላለች።
የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባል ቤኒ ጋንዝ የዋሽንግተን ቆይታቸውን አጠናቀው ዛሬ ለንደን ይገባሉ።
በዚሁ ወቅትም እስራኤል በጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ ተደራሽነት ዙሪያ በያዘችው አቋም የብሪታንያ ትዕግስት እያለቀ መሆኑን እንደሚነግሯቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሮን ገልጸዋል።
ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት በጋዛ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርሶ ያለምንም ተጽዕኖ ለፍልስጤማውያን ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው እየጠየቁ ነው።
በካይሮ ለሶስት ቀናት ከሃማስ ጋር ሲካሄድ የቆየውን ድርድር ተከትሎ ይጠበቅ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት አልተደረሰም።
የፍልስጤሙ ቡድን ባቀረበው የተኩስ አቁም እቅድ ዙሪያም የእስራኤል ምላሽ አልተሰማም።