በካን ዩኒስ ከ280 በላይ ሰዎች የተቀበሩበት የጅምላ መቃብር ተገኘ
የእስላማዊ ትብብር ድርጅት በህክምና ተቋም ውስጥ የተገኘው የጅምላ መቃብር እስራኤል በጋዛ የጦር ወንጀል መፈፀሟን ያረጋግጣል ብሏል
ድርጅቱ አለማቀፉ ማህበረሰብ "የእስራኤልን የጋዛ ወረራ" እንዲያስቆም ጠይቋል
የእስላማዊ ትብብር ድርጅት (ኦአይሲ) እስራኤል በጋዛ "አሰቃቂ ጭፍጨፋ" እየፈፀመች ነው አለ።
በካን ዩኒስ ናስር ሆስፒታል ውስጥ የ283 ሰዎች አስከሬን በጅምላ ተቀብሮ መገኘቱ ተገልጿል።
እስራኤል ለአራት ወራት ውጊያ ካደረገችበት ካን ዩኒስ ከሁለት ሳምንት በፊት መውጣቷን ተከትሎ ነው የጅምላ መቃብሩ በናስር የህክምና መስጫ ማዕከል የተገኘው።
መቀመጫውን ሳኡዲ አረቢያ ያደረገው የእስላማዊ ትብብር ድርጅት ባወጣው መግለጫ የጅምላ መቃብሩ “እስራኤል በሆስፒታሉ የተጠለሉና በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮችና ታማሚዎችን አሰቃይታ መግደሏን ያመላክታል” ብሏል።
በህክምና ተቋሙ ውስጥ የተገኘው የጅምላ መቃብር “የጦር ወንጀል፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀልና የተደራጀ የመንግስት ሽብርተኝነት” መፈጸሙን እንደሚያሳይም ጠቁሟል።
ይህ ድርጊት ምርምራና ተጠያቂነት ይፈልጋል ያለው የእስላማዊ ትብብር ድርጅት፥ እስራኤል በአለማቀፉ የወንጀል ህግ ማዕቀብ ሊጣልባት እንደሚገባም አሳስቧል።
አለማቀፉ ማህብረሰብ በተለይም የጸጥታው ምክርቤት “እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምትፈጽመውን ወረራና የጦር ወንጀል” እንዲያስቆሙም በድጋሚ ጥሪውን አቅርቧል ሲል አናዶሉ ዘግቧል።
እስራኤል በአለማቀፉ የፍትህ ፍርድቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ እንደተመሰረተባት ይታወሳል።
ቴል አቪቭ ንጹሃንን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶቿን እንድታቆምና የሰብአዊ ድጋፎች ያለገደብ እንዲገቡ እንድትፈቅድ ውሳኔ መተላለፉም አይዘነጋም።
የጸጥታው ምክርቤትም በጋዛ በአስቸኳይ ተኩስ እንዲቆም ውሳኔ ቢያሳልፍም ሰባተኛ ወሩን የያዘውና ከ34 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት እስካሁን አልቆመም።