“በ21ኛው ክፍለ ዘመን በጅምላ መራብን ልንቀበል አንችልም” - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
በምድራችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የረሃብ አደጋ ከተጋጠባቸው አከባቢዎች ምስራቅ አፍሪካ አንዱ መሆኑ ይታወቃል
ጉቴሬዝ፤ ቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት 2023 የከፋ ረሃብ የሚከሰትበት ሊሆን ይችላል ብለዋል
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የጅምላ ረሃብን መቀበል አንችልም ሲሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተናገሩ፡፡
ዋና ጸሃፊው “በዚህ ዓመት የከፋ ርሃብ ሊከሰት ይችላል የሚል የተረጋገጠ ስጋት አለ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፋቸው አስታውቀዋል፡፡
ቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት 2023 ደግሞ የከፋ ሊሆን ይችላልም ብለዋል ጉቴሬዝ።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የጅምላ ረሃብን መቀበል እጅግ ከባድ ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፤ አደጋውን ለማቃለል የተቀናጀ የባለብዙ ወገን ምላሽ እንዲሁም ጠንካራ የፖለቲካ እና የግሉ ዘርፍ አመራር እንፈልጋለን ብለዋል።
በምድራችን ላይ ከፍተኛ የሆነ የረሃብ አደጋ ከተጋጠባቸው አከባቢዎች ምስራቅ አፍሪካ አከባቢ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የድርጅቱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በቀጠለው ድርቅ ሳቢያ በርካቶች ለረሃብ እየተጋለጡ ነው ብሏል፤ በሀገራቱ 13 ሚሊየን ሰዎች ለከፋ ረሃብ አደጋ መጋለጣቸውን በመጠቆም።
የግብርና ስራዎችን አለመስራት እንዲሁም የምግብ እጥረት በርካቶች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ያለው ድርጅቱ፤ በቀጠናው ሊደርስ የሚችለውም የሰብዓዊ ቀውስ ለመግታት አስቸኳይ ድጋፎችን ያስፈልጋሉ ማለቱም አይዘነጋም።
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመዝነቡ ሳቢያ ድርቁ መቀጠሉንም ነው ድርጅቱ ያስታወቀው።
በዚህም የእርሻ ስራ ከመቆሙም በላይ የቀንድ ከብቶች እየሞቱ ነው ያለው ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የሚገኙ 13 ሚሊየን ሰዎች ከረሃብ አፋፍ ላይ ደርሰዋል ብሏል።
በሀገራቱ አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፎች ካልተደረጉ ሊያጋጥም የሚችለውን ሰብአዊ ቀውስ ማስቆም ሊያዳግት እንደሚችልም አሳስቧል።
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ የሚሆን 327 ሚሊየን ገንዘብ እንደሚያስፈልገውም ነው ፕሮግራሙ ያስታወቀው።