እስራኤል በግንቦት ወር የአልጀዚራን ቢሮ ዘግታ ስርጭት እንዲያቋርጥ ማድረጓ ይታወሳል
የፍልስጤም አስተዳደር አልጀዚራ በዌስትባንክ ስርጭት እንዳያደርግ በጊዜያዊነት አግዷል።
የኳታሩ ቴሌቪዥን የታገደው "ግጭት ቀስቃሽ እና አሳሳች ዘገባዎችን እያቀረበ ነው፤ በፍልስጤም የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ነው" የሚል ክስ ቀርቦበት መሆኑን የፍልስጤም ዜና አገልግሎት ዋፋ ዘግቧል።
ሁሉም የአልጀዚራ ጋዜጠኞች በፍልስጤም ይዞታዎች ስር እንዳይሰሩ የተከለከሉ ሲሆን፥ በራማላህ የሚገኘው የቴሌቪዥን ጣቢያው ቢሮ እንዲዘጋ ትዕዛዝ መተላለፉንም አሶሼትድ ፕረስ ያነጋገራቸው የጣቢያው ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
አልጀዚራ እና በፋታህ የሚመራው የፍልስጤም አስተዳደር ግንኙነት ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የሻከረው የቴሌቪዥን ጣቢያው የፍልስጤም የጸጥታ ሃይሎች በጀኒን ከታጣቂዎች ጋር መዋጋታቸውን ከዘገበ በኋላ ነው።
የፕሬዝዳንት ማህሙድ አባስ አስተዳደር የኳታሩ ቴሌቪዥን ለዚህ ጉዳይ ሽፋን መስጠቱ "በፍልስጤም የውስጥ ጉዳይ" ጣልቃ እንደመግባት ተመልክተውታል።
በዶሃ የሚገኘው የአልጀዚራ ዋና ቢሮ ባወጣው መግለጫ የፍልስጤም አስተዳደር ያሳለፈውን ውሳኔ ያወገዘ ሲሆን "ውሳኔው በጀኒን ያለውን ሀቅ ተሸፋፍኖ እንዲቀር ለማድረግ ያለመ ነው" ብሏል።
በጋዜጠኞቹ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲደርስ መቆየቱን በመጥቀስም ለፍልስጤም አስተዳደር የሙያውን ስነምግባር አክብሮ እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ማረጋገጡን ገልጿል።
በራማላህ የሚገኘው የፍልስጤም የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ማዕከል የፋታህን ውሳኔ "ለፕሬስ ነጻነት ላይ የተቃጣ አሳፋሪ ጥቃት ነው" ብሎታል።
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስም አልጀዚራ እንዲዘጋ መወሰኑ "ሀገወጥ እና ኢምክንያታዊ" ነው ማለቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
እስራኤል በግንቦት ወር “የሃማስ አፈቀላጤ ነው፤ የእስራኤልን ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል” ያለችውን አልጀዚራ ቢሮውን እንዲዘጋና በሀገሪቱ ከሳተላይት ላይ እንዲወርድ ማድረጓ ይታወሳል።
ኳታር በፈረንጆቹ 1996 ያቋቋመችው አልጀዚራ ለመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ሰፊ ሽፋን በመስጠት ይታወቃል።
ከ45 ሺህ 500 በላይ ፍልስጤማውያን ያለቁበትን፤ ከ100 ሺህ በላይ የቆሰሉበትንና ሚሊየኖች ለተደጋጋሚ መፈናቀል የተዳረጉበትን የጋዛ ጦርነት በየእለቱ መዘገቡም በኔታንያሁ አስተዳደር አልተወደደም።
አልጀዚራ በእየሩሳሌም የሚገኘው ቢሮአ ተዘግቶና ንብረቶቹ ተወርሰው የጋዛን ጉዳይ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ለማስተላለፍ መገደዱ የሚታወስ ነው።