“ከፍልስጤማውያን ጋር ለመነጋገር ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው”- የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር
እስራኤል ከዚህ ቀደም ከአረብ ሀገር ጋር የመጨረሻ የሰላም ስምምነት ያደረገችው ከ26 ዓመታት በፊት ከፍልስጤም ጋር ነው
የሚኒስትሩ መግለጫ እስራኤል ከዩኤኢ እና ከባህሬን ጋር ከምትፈራረመው ስምምነት ጋር ተያይዞ የወጣ ነው
“ከፍልስጤማውያን ጋር ለመነጋገር ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው”- የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቤኒ ጋንትዝ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ ከፍልስጤም ጋር እንደገና ድርድርን መጀመር አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ “ለድርድር ለመቀመጥ ጊዜው አሁን ነው” ብለዋል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር የሰጡት መግለጫ በአሜሪካ መዲና ዋሽንግተን በዋይት ሀውስ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፣ በባህሬን እና በእስራኤል መካከል ከሚፈረመው የሰላም ስምምነት ጋር ተያይዞ የወጣ ነው፡፡
ጋንትዝ አያይዘውም “የፍልስጤም እና የእስራኤል የፀጥታ ትብብር እንደገና ሊጀመር ይገባል” ብለዋል፡፡
ጋንትዝ በአሁኑ ወቅት በፍልስጤም በኩል በደህንነት ግንባር ላይ ችግር እንዳልተመለከቱም ጋንትዝ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና እስራኤል እንዲሁም በእስራኤል እና በባህሬን መካከል በሚደረገው የሰላም ስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲሳተፉ ኋይት ሀውስ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስም ከ 1 ሺህ በላይ የአሜሪካ ፣ የአረብ እና ዓለም አቀፍ ግለሰቦችን ጋብዟል፡፡
የፊርማው ዝግጅት እና ታዳሚያን-ዋይት ሀውስ
በፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት እና እስራኤል መካከል እ.ኤ.አ. በ 1993 የኦስሎ ስምምነት ከተፈረመ ከ 26 ዓመታት በላይ ቖይታ በኋላ ዛሬ በዋይት ሃውስ በእስራኤል እና በአረብ ሀገራት መካከል የሚደረገው የሰላም ስምምነት ፊርማ የመጀመሪያው ነው፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና የባህሬን መንግሥት በፊርማው ሥነ-ስርዓት ላይ በቅደም ተከተል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና አብዱል ላቲፍ ቢን ራሺድ አል ዛያኒ የተወከሉ ሲሆኑ እስራኤል ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ተወክላለች፡፡