ወላጆች ተመድ ልጆቻቸውን ትግራይ ክልል ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመልስላቸው ጠየቁ
ግጭቱ ከአማራና ትግራይ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች አልፎ ወደ አፋር ክልል ተስፋፍቷል
ወላጆች ልጆቻቸው ከዩኒቨርሲቲዎቹ እንዲመለሱ ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ ነው
በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ልጆች ያሏቸው ወላጆች፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ልጆቻቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻችላቸው በሰልፍ ጠይቀዋል፡፡
በትግራይ ክልል በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመደቡ ተማሪዎች እንዲመለሱላቸው ቤተሰቦቻቸው በሰልፍ ጠይቀዋል፡፡
የተማሪዎች ወላጆች በዛሬው እለት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ)በአፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን(ኢሲኤ) መሰብሰቢያ አዳራሽ ፊት ለፊት ተሰልፈዋል፤ ተመድም ልጆቻቸው የሚመለሱበትን መንገድ እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡
ትግራይ ክልል ባለው ግጭት ሳቢያ ስጋት ያደረባቸው ወላጆች ከተመድ በተጨማሪ መንግስት በትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ባሉ በተማሪዎቹ ዙሪያ እልባት እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ እየጠየዉ ይገኛሉ፡፡
ሰልፍ ያደረጉት ወላጆች፤መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን በሰልፉ አንስተዋል፤ ነገርግን አሁንም ልጆቻችን ይመለሱ የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የተማሪዎች ወላጆች ልጆቻቸው ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመለሱ ጥያቄ ማቅረብ የጀመሩት የኢትዮጵያ መንግስት የተናጠል ተከስ አቁም አውጆ፤ መከላከያ ሰራዊትን ከትግራይ ማስወጣቱን ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ት/ምሚኒስቴር በወቅቱ “ከየዩኒቨርስቲዎቹ አመራሮች እና ከዓለም አቀፍ ተራድኦ ተቋማት ጋር በመሆን ጉዳዩን እየሰራበት ይገኛል፡፡ በተደረገው ጥረትም የዩኒቨርቲዎችን አመራር ለማግኘት የተቻለ ሲሆን ተማሪዎች በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና የሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ያሉም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል” ሲል ለወላጆች ጥያቄ መልስ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው በትግራይ ሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል ለሚሉ አካላት ለማሳየትና ተጨማሪ ኪሳራ ሳይደርስ የትግራይ ቀውስ በውይይት እንዲፈታ በማቀዱ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
የመንግስት ጦር መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌንና ሌሎች ከተሞችን መቆጣጠራቸውን ሮይርስ ዘግቦ ነበር፤ የህወሓት ኃይሎች ለወራት በአማራ ክልል ስር የነበሩት ኮረምና አላማጣን መልሶ ለመቆጣጠር መቻሉም ተዘግቧል፡፡
ግጭቱ ከአማራና ትግራይ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች አልፎ ወደ አፋር ክልል ተስፋፍቷል፤ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የደቡብና የሲዳማ ክልልን ጨምሮ ሌሎች ክልሎች መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ የጸጥታ ሃይላቸውን ወደ ስፍራው አሰማርተዋል።