በፕሬዝዳንት ትራምፕ የድንበር ፖሊሲ ከወላጆቻቸው የተለዩ የ545 ልጆች ወላጆቻቸው ሊገኙ አልቻሉም
አሁን ላይ ወላጆችን የማፈላለግ ስራ በመከናወን ላይ ነው
ትራምፕ ህገወጥ ስደትን ለመከላከል በወሰዱት እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ከወላጆቻቸው ተለይተዋል
በፕሬዝዳንት ትራምፕ የድንበር ፖሊሲ ከወላጆቻቸው የተለዩ የ545 ልጆች ወላጆቻቸው ሊገኙ አልቻሉም
ስደተኛ ጠል እንደሆኑ የሚነገርላቸው እና እርሳቸውም ይህንኑ በተደጋጋሚ ያቀነቀኑት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ መሪነት እንደመጡ ብዙም ሳይቆዩ ነበር በድንበር ላይ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ትዕዛዝ የሰጡት፡፡
የአሜሪካን ድንበር አቋርጠው በሜክሲኮ በኩል የሚገቡ ስደተኞች ላይ ከባድ የሚባል እርምጃ በመውሰድ ወላጆችን ከልጆቻቸው መለየትን ፍልሰትን ለማስቆም እንደሁነኛ አማራጭም ተጠቅመውበታል፡፡
ህጻናትን ከወላጆቻቸው የመለየቱን ተግባር በፖሊሲ ለማስደገፍ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የሙከራ መርሃ ግብር ያሉት ትዕግስት የለሽ ፖሊሲ (Zero Tolerance Policy) ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ፖሊሲው እ.ኤ.አ. 2018 ግንቦት ወር ላይ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ በዚህ ፖሊሲ ምክንያት 2,342 ስደተኛ ልጆች ከወላጆቻቸው እንዲነጠሉ የተደረገ ሲሆን ፖሊሲው ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በነበሩት ጥቂት ወራት ከወላጅ ተነጥቀው እንዲለያዩ ከተደረጉት ጋር በድምሩ 4,100 ልጆች ያለወላጅ በማሳደጊያ ማዕከላት እንዲሆኑ ሲደረጉ ወላጆቻቸው አንድም ወደመጡበት ሀገር ተመልሰዋል አሊያም ለእስር ተዳርገዋል፡፡
ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 10 ቀን 2013 ዓ.ም በወጣ አንድ መግለጫ ከወላጆቻቸው እንዲለዩ ከተደረጉት ልጆች መካከል የ545ቱ ህልጆች ወላጆቻቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ የፍትሐብሔር ነፃነት ህብረት (ACLU) “የ 545 ልጆች ወላጆች - በትራምፕ አስተዳደር ጭካኔ የተሞላበት የቤተሰብ መለያየት ተግባር በግዳጅ ከተለዩ በኋላ እስካሁን እንዳልተገኙ ለፍርድ ቤት ሪፖርት አድርገናል” ሲል በትዊተር አድራሻው አሳውቋል፡፡
እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ አሜሪካ ፖሊሲ ቀርጻ ልጆችን ከወላጆቻቸው መለየት የመጀመሯ ዜና በወቅቱ በሀገሩስጥም በውጭም ከፍተኛ ትችት አስከትሎ ነበር፡፡
ፖሊሲው ተግባራዊ ከሆነ ከ6 ሳምንታት በኋላ ግን በህገወጥ መንገድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ወላጆች ልጆቻቸውን አደጋ ላይ እስካልጣሉ ድረስ ቤተሰብን አስተዳደራቸው የመለያየት ተግባሩን እንደሚያቆም ገለጹ፡፡
አብዛኛው መገኘት ያልቻሉ ወላጆች ወደመጡበት ተመልሰው (ዲፖርት ተደርገው) ሊሆን እንደሚችል ይታመናል ብሏል ሲኤንኤን ባወጣው ዘገባ፡፡
ወላጆቹን ለማግኘት ብዙ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ የአሜሪካ የፍትሐብሔር ነፃነት ህብረት አሳስቧል፡፡ ምንም እንኳን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታዎችን ፈታኝ ቢያደርግም የጠፉትን ወላጆች የማፈላለግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡