ፓሪስ ከተማ ከ37 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ህንጻዎች እንዳይገነቡ ከለከለች
ፓሪስ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው የከተማዋ ውበት በረጃጅም ህንጻዎች ምክንያት እንዳይጠፋ በሚል ነው
የከተማዋ ነዋሪዎች በአዲሱ ህግ ምክንያት ለሁለት ተከፍለዋል ተብሏል
ፓሪስ ከተማ ከ37 ሜትር በላይ ከፍታ ያላቸው ህንጻዎች እንዳይገነቡ ከለከለች፡፡
በዓለማችን ካሉ ውብ እና ተወዳጅ ከተሞች መካከል አንዷ የሆነችው ፓሪስ ውበቷን ይዛ ለመቀጠል በሚል የህንጻዎችን ርዝመት ገድባለች፡፡
ከተማዋ ከፈረንጆቹ 1977 ጀመሮ ከ37 ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ህንጻዎች እንዳይገነቡ ህግ አውጥታ የነበረ ቢሆንም የህን ህግ በ2010 ሰርዛ ነበር፡፡
የቀድሞ የፓሪስ ከንቲባ በርትራንድ ዴላኖ በ2010 የቀደሞውን ህግ በመሻር በከተማዋ እስከ 180 ሜትር ርዝመት ያላቸው ህንጻዎች እንዲገነቡ ሌላ ህግ ማውጣታቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ይህ አዲስ ህግ መውጣቱን ተከትሎ በፓሪስ አልፎ አል3ፎ ብቻቸውን ወደ ሰማይ የወጡ ህንጻዎች መገንባታቸው የከተማዋን ውበት አጥፍቶታል በሚል ትችቶች ሲቀርቡ ቆይተዋል ተብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም ፓሪስ ከ50 ዓመት በፊት አውጥታው ወደ ነበረው ህግ መመለሷን የገለጸች ሲሆን በከተማዋ ከ37 ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ህንጻዎች እንዳይገነቡ በድጋሚ ከልክላለች፡፡
ጉዳዩ የፓሪስ ከተማ ነዋሪዎችን ለሁለት ከፍሎ እያከራከረ ሲሆን የተወሰኑት ህጉ ለከተማዋ ውበት ጥሩ ሲሉ ገሚሶቹ ደግሞ ፓሪስ በዚህ ህግ ምክንያት ከእኮዮቿ ለንደን እና ኒዮርክ ጋር ስትነጻጸር ተመራጭነቷን ይቀንሳል በማለት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
ፓሪስ ወደ ቀድሞ ህጓ መመለሷ ለአየር ንብረት ለውጥ የሰጠችው ትኩረትን ያሳያል የተባለም ሲሆን የአዳዲስ ህንጻዎች ግንባታ የአየር ብክለትን ይጨምራሉ ሲሉም እየተከራከሩበትም ነው፡፡
ለንደን ቅጥ ባጡ ረጃጅም ህንጻዎች ውበቷን እያጣች ነው በሚል ፈረንሳዊያን የዋና ከተማቸውን ውሳኔ ሲደግፉ ሌሎቹ ደግሞ በዚህ ህግ ምክንያት ፓሪስ ውዳቂ እና ያልለማች ከተማ ያስብላታም ብለዋል፡፡