አንደኛውን የአለም ጦርነት የሚያስታውሱት ፈረንሳዊት በ118 አመታቸው አረፉ
በአለማችን የእድሜ ባለጠጋ ሉሲል ራንደን በፈረንጆቹ 1904 ነበር የተወለዱት
ራንደን በ2022 በህይወት ያሉ የእድሜ ባለጠጋ በሚል በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ መስፈራቸው ይታወሳል
የአንደኛውን የአለም ጦርነት ሲጀመር የ10 አመት ታዳጊ የነበሩት ፈረንሳዊት መነኩሴ ሉሲል ራንደን በ118 አመታቸው ህይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።
እህት አንድሬ በሚለው ስማቸው የሚታወቁት ራንዳን፥ በቱልሰን ከተማ እንቅልፍ ላይ እንዳሉ ማረፋቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
ራንዳን በፈረንጆቹ የካቲት 11 1904 በደቡባዊ ፈረንሳይ ሲወለዱ ኒውዮርክ የመጀመሪያውን የምድር ውስጥ ባቡሯን ስራ አስጀምራለች፤ የቱር ደ ፍራንስ የብስክሌት ውድድርስም ከተጀመረ ገና አንደኛ አመቱ ነበር።
የአንደኛው የአለም ጦርነት በ1914 ተጠናቆ ሁለት ወንድሞቻቸው ሲመለሱም በደምብ ያስታውሳሉ።
የካቶሊክ እምነትን በ26 አመታቸው ተቀብለው በ41 አመታቸው የመነኮሱት የእድሜ ባለጠጋ ለ31 አመታት በቪቼ ሆስፒታል አገልግለዋል።
ከሆስፒታል በጡረታ ከወጡ በኋላም አዛውንቶችን የሚንከባከብ ማዕከል ከፍተው ደግነትን በብዙው አሳይተዋል።
ይህ መልካምነታቸውም በ2021 የኮቪድ 19 ወረርሽኝ 81 የማዕከሉ ነዋሪዎችን ሲያጠቃ እሳቸውን በሩቁ እንዲያልፍ ማድረጉን ያምናሉ።
“ሰዎች ስራ ይገድላል ብለው ያምናሉ፤ ለእኔ ግን ስራ ነው እስካሁን በህይወት ያቆየኝ፤ 108 አመት እስኪሞላኝ ሳልታክት ሰርቻለሁ” ሲሉ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ተናግረዋል።
እህት አንድሬ ምንም እንኳን የአይን ብርሃናቸውን አጥተው በዊልቸር መንቀሳቀስም ግድ ቢሆንባቸውም ከእሳቸው በእድሜ ዝቅ ያሉትን አዛውንቶች መንከባከብ ያዘወትሩ ነበር።
“ሰዎች ከመጠላላት ይልቅ እርስ በርስ መዋደድና መረዳዳት አለባቸው፤ ያለንን ሁሉ ካካፈልን ሁሉም መልካም ይሆናል” ነበር ያሉት።
የካቶሊክ መነኩሴዋ የእድሜያቸውን ትክክለኝነት ለማረጋገጥ የጸጉራቸውን ዘለላ ወይም የዘረመል ናሙና ለመውሰድ ተጠይቀው፥ “የእድሜዬን ጉዳይ ፈጣሪዬ ብቻ ነው የሚያውቀው” ብለው ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ሉሲል ራንደን ፥ ጃፓናዊቷ ኬን ታንካ ባለፈው አመት በ119 አመታቸው ካረፉ በኋላ በህይወት ያሉ የእድሜ ባለጠጋ ተብለው በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ መስፈራቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ራንዳን ከነአለም ጦርነት ትዝታቸው በማረፋቸውም በፈረንሳይ በህይወት ያሉ የእድሜ ባለጠጋ ክብርን የ112 አመቷ ማሪ ሮስ ቴሰር ይይዛሉ ተብሏል።
ከቴሰር በላይ እድሜ የሚኖራቸው ነገር ግን በይፋ ያልታወቁ ሰዎች እንደሚኖሩ ግን ይገመታል።
በፈረንጆቹ 1997 በደቡባዊ ፈረንሳይ አርልስ ያረፉት ጃኔ ካልመንት 122 አመታትን በምድር ላይ በመኖር ክብረወሰን መያዛቸው ይነገራል።