ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ በኦሊምፒኩ 47ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች
የ33ኛው የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ትናነት ምሽት በስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም በደማቅ ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
በግዙፉ የፈረንሳይ በስታድ ደ ፍራንስ ብሔራዊ ስታዲየም በተካሄደው የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይም አትሌቶች በመሮጫ መሙ ላይ በማለፍ ስንብት አድርገዋል።
በዘንድሮው ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በወንዶች ማራቶን ያስገኘው አትሌት ታምራት ቶሎና በሴቶች ማራቶን የብር ሜዳሊያ ያገኘችው አትሌት ትዕግስት አሰፋ የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለቡ በተመልካቾችና እንግዶች ፊት አልፈዋል።
የሴቶች ማራቶን የሜዳሊያ ስነ ስርዓትም በመዝጊያው ላይ የተካሄደ ሲሆን፤ አትሌት ትእግስት አሰፋ የብር በሜዳሊያዋን ተረክባለቸ።
በመርሐ ግብሩ የኦሎምፒክ ባንዲራ 34ኛውን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እ.አ.አ በ2028 ለሚካሄድበት ሎስ አንጀለስ የውድድር አዘጋጆች የማስረከብ ስነ ስርዓትም ተካሂዷል።
ታዋቂው የሆሎውድ የፊልም ተዋናይ ቶም ክሩዝ የኦሎምፒክ ስንደቅ ዓላመውን ከተረከበ በኋላ በሞተር ሳይክ ከስታዲየሙ ሲወጣም ታይቷል።
አሜሪካዊው ታዋቂ ራፐር ስኖፕ ዶግና አሜሪካዊቷ ድምጻዊ ቢሊ ኤሊሽን ጨምሮ የዓለማችን ታዋቂ ሙዚቀኞች በስታድ ደ ፍራንስ ስታዲየም የሚያቀርቡት ስራ ለመዝጊያ ስነ ስርዓቱ ድምቀት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ በአትሌቲክስና ውሃ ዋና 38 ስፖርተኞች አሳትፋለች። 1 የወርቅና 3 የብር በድምሩ 4 ሜዳሊያዎችን በማግኘት 47ተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
አሜሪካ በኦሊምፒኩ አንደኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች። ቻይና፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያና አዘጋጇ ፈረንሳይ ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።