በኦሎምፒክ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ቦትስዋና ብሄራዊ በዓል አወጀች
ቦትስዋናዊው አትሌት ሌትሴሌ ቴቦጎ በ200 ሜትር ሩጫ ለሀገሩ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል
የቦትስዋና ፕሬዝዳንት ድሉን ተከትሎ አርብ ከሰዓት መደበኛ የስራ ቀን መሆኑ ቀርቶ ብሄራዊ በዓል እንዲሆን አውጀዋል
ቦትስዋና በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳያ ምገኘቷን ተከትሎ ብሄራዊ በዓል ማወጇ ተሰምቷል።
የቦትስዋና ፕሬዝዳንት የሀገሪቱ አትሌት ሌትሴሌ ቴቦጎ በፓሪስ ኦሎምፒክ በ200 ሜትር ሩጫ አንደኛ በመሆን በማጠናቀቅ ለሀገሩ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቱን ተከትሎ ድሉን ለማክበር አርብ ከሰዓት ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር በይፋ አውጀዋል።
ቦትስዋናዊው አትሌት ሌትሴሌ ቴቦጎ ትናንት ምሽት በፓሪስ ኦሎምፒክ የተካሄደውን የ200 ሜትር ሩጫ አሜሪካውያኑን ኬኒ ቤድናሪክ እና ኖዋህ ሌይልስን በመርታት በርቀቱ ያሸነፈ የመጀመሪያው አፍሪካው አትሌት መሆን ችሏል።
በዚህም ለሀገሩ በኦሎምፒክ ታሪክ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ሌትሴሌ ቴቦጎን፤ የዓለማችን 5ኛው ፈጣኑ ሰው መሆን መቻሉም ነው የተነገረው።
የቦትስዋና ፕሬዝዳንት ሞክዌትሲ ማሲሲሰ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ በቦትዋና ዜጎች ስም የተሰማቸውን ድስታ የገለጹ ሲሆን፤ በህይወት የሌሉትን የአትሌት ሌትሴሌን እናትም አመስግነዋል።
የአትሌት ሌትሴሌ ድል በሪፐብሊኩ የታሪክ መዝገብ ላይ በልዩ መልኩ በሚሰፍር እጅግ ልዩ፣ ተገቢ እና ኃላፊነት የተሞላበት መንገድ ቆም ብሎ ሊከበር የሚገባ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት አርብ ከሰዓት መደበኛ የስራ ቀን መሆኑ ቀርቶ የቦትስዋና ብሄራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር መወሰናቸውንም ነው ፕሬዝዳንቱ ያስታወቁት።
ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም የሀገሪቱ ፓርላማ ድሉን አስመልክቶ የለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን፤ አትሌት ሌትሴሌ ቦትሰዋናንና አፍሪካን ማኩራቱን በማውሳት እውቅና በመስጠት ይገባል ብሏል።
ፓርላማው በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ውሳኔ መሰረት ዛሬ ከሰዓት በኋላ እንደ ብሔራዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር እና መደበኛ የስራ ቀን መሆኑ እንዲቀር ውሳኔ አሳልፏል ነው የተባለው።
አትሌቱ ቦትስዋና ውስጥ በፈለገው ቦታ ባለ 5 መኝታ ትልቅ መኖሪያ ቤት በሀገሪቱ መንግስት ወጭ እንዲሰራለት ውሳኔ ያሳለፈ አሳልፏል።
የቦትስዋና የወጣቶች ሚንስትር ራክጋሬ በበኩላቸው ከተለያዩ አካላት ቃል የተገቡ ሌሎች የገንዘብ እና የአይነት ሽልማቶች እንደተጠበቁ ሆኖ የሀገሪቱ መንግስት የ10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለመሸለም መወሰኑን አስታውቀዋል።