የወንዶች እግርኳስ ጨዋታ ከ1896 እና 1932 ውጭ የኦሎምፒክ ውድድሮች አካል ሆኖ ሲካሄድ ቆይቷል
የ2024ቱ የፓሪስ ኦሎምፒክ አርብ በይፋ ከመከፈቱ አስቀድሞ በነገው እለት የኦሎምፒክ የእግርኳስ ግጥሚያዎች ይጀመራሉ።
በምድብ ሁለት የተደለደሉት አርጀንቲና እና ሞሮኮ የሚያደርጉት ጨዋታም ይጠበቃል።
የኦሎምፒክ ውድድር ከተጀመረ አንስቶ (ከ1896 እና 1932 ውጭ) የወንዶች የእግርኳስ ጨዋታዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
16 ብሄራዊ ቡድኖች በአራት ምድብ ተደልድለው በሚጫወቱበት ፍልሚያ የሚያሸንፈው ቡድን ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የኦሎምፒክ ሜዳልያ ያገኛል።
በወንዶች የኦሎምፒክ እግርኳስ የሚሳተፉ ቡድኖች እድሜያቸው ከ23 አመት በታች የሆኑ ተጫዋቾችን ነው የሚያሳትፉት። ሶስት ከ23 አመት በላይ ተጫዋቾችን እንዲያካትቱ ግን ይፈቀድላቸዋል።
በፓሪሱ የኦሎምፒክ እግርኳስ የኮፓ አሜሪካን ለ16ኛ ጊዜ ያነሳችው አርጀንቲና ትጠበቃለች።
በቀድሞው የአርሰናል ኮከብ ቴሪ ሄነሪ የሚሰለጥነው የፈረንሳይ የኦሎምፒክ የእግርኳስ ቡድንም የወርቅ ሜዳልያውን ለማጥለቅ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የ2024ቱ የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮኗ ስፔንም በፓሪስ ከሚጠበቁት መካከል ትጠቀሳለች።
ብራዚል በወንዶች እግርኳስ በርካታ የኦሎምፒክ ሜዳልያ በማግኘት (ሰባት) ቀዳሚ ናት፤ ሀንጋሪ እና ብሪታንያ ደግሞ ሶስት ጊዜ አሸንፈዋል።