
ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች በ6 አትሌቶች ትወከላለች
17ኛው የፓራሊምፒክ ዛሬ መከናወን ሲጀምር በ22 የስፖርት አይነቶች 4400 አትሌቶችን ያሳትፋል፡፡
በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ከስታዲየም ውጪ ፕሌስ ዴ ላ ኮንኮርድ እና በሻምፕ ኢሊዜ በተባሉ ታዋቂ የህዝብ ጎዳናዎች ላይ በትላንትናው እለት ተከናውኗል፡፡
የፓራሊምፒክ ውድድር ለመጀመርያ ጊዜ መካሄድ የጀመረው በ1960ቱ የሮም ኦሎምፒክ ነበር። በዚሁ አመት ከ23 ሀገራት የተውጣጡ 400 በዊልቼር የሚንቀሳቀሱ አትሌቶች ሲሳተፉ በወቅቱ በስምንት ውድድሮች 57 ሜዳሊያዎች ተዘጋጅተው እንደነበርም መረጃዎች ያወሳሉ፡፡
ቀጣይ በነበሩ ውድድሮች የራሱን ዘርፍ አግኝቶ የተሳታፊዎችን ቁጥር እያሳደገ የመጣው ውድድሩ በ2012ቱ የለንደን ኦሎምፒክ 164 ሀገራትን በማሳተፍ ከፍተኛ ቁጥርን ይዟል፡፡
ሆኖም በዘንድሮው የፓሪሱ ውድድር የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ከዚህ ቀደም ከነበሩት ተሳታፊዎች ቁጥሩ ብልጫ እንዳለው ተነግሯል፡፡
ለ11 ቀናት የሚካሄደው የፓሪስ ፓራሊምፒክ ውድድር ከ168 ሀገራት የተውጣጡ አትሌቶች፣ 8 የስደተኛ ቡድኖች እና ሁለት ገለልተኛ ተወዳዳሪዎችን ያሳትፋል፡፡
ጠረጴዛ ቴንስ ፣ ባድሜንተን ፣ ሩጫ ፣ ቅርጫት ኳስ ፣ የእጅ ኳስ ፣ ዋና እና ቴክዋንዶን ጨምሮ በ22 ውድድሮች አትሌቶች ለ549 የወርቅ ሜዳልያዎች ይፋለማሉ፡፡
ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች በስድስት አትሌቶች የምትወከል ሲሆን ልዑካን ቡድኑ ነሐሴ 19 ቀን 2016 ዓ.ም ወደ ፓሪስ አቅንቷል።
የኢትዮጵያ አትሌቶች በ1 ሺ 500 ሜትር በአራት የአካል ጉዳት ዘርፎች ይወዳደራሉ።
አትሌት ያየሽ ጌቴ በአይነስውር (T-11 የውድድር ዘርፍ) እንዲሁም በቶኪዮ በተካሄደው ፓራሊምፒክ በውድድሩ ታሪክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣችው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በጭላንጭል (T-13 የውድድር ዓይነት) ይሳተፋሉ፡፡
በወንዶች አትሌት ይታያል ስለሺ ይግዛው በአይነስውር ጭላንጭል (T-11)፣ በእጅ ጉዳት (T-46 ምድብ) አትሌት ገመቹ አመኑ ኢትዮጵያን ወክሎ ይወዳደራል።
በተጨማሪም አትሌቶቹን የሚደግፉ ሁለት አሯሯጭ አትሌቶች ይሳተፋሉ።
50 ሺህ ተመልካቾች ይታደሙበታል ተብሎ የሚጠበቀው ውድድር 300 ሚሊየን የቴሌቪዥን ተመልካቾች እንደሚኖሩት የተነገረ ሲሆን የመዝጊያ ፕሮግራሙ ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም ይደረጋል፡፡