የፈረንሳይ መንግስት ከቢጫ ሰደርያ ለባሾች ተቃውሞ በኋላ ከባድ ፈተና ገጥሞታል ተብሏል
የፓሪስ ፖሊስ እና ተቃዋሚዎች ለሶስተኛ ጊዜ ተፋጠዋል።
የፓሪስ ፖሊስ ከተቃዋሚዎች ጋር ለሶስተኛ ጊዜ ተጋጭቷል።
በሽህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በመላው ፈረንሳይ የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የጡረታ እድሜ ማሻሻያ በመቃወም ያደረጉት ሰልፍ ውጥረት አንግሷል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው አለመረጋጋት እና የስራ ማቆም አድማ ፕሬዝዳንት ማክሮን ከአራት ዓመታት በፊት "ቢጫ ሰደርያ ለባሾች" እየተባለ ከሚጠራው ተቃውሞ በኋላ በስልጣናቸው ላይ ከባድ ፈተና እንዲገጥማቸው አድርጓቸዋል ነው የተባለው።
"ማክሮን ስልጣን ይልቀቁ!" እና "ማክሮን ሊወድቁ ነው፣ እናሸንፋለን" የሚሉ መልዕክቶችን ያነገቡ ሰልፈኞች በደቡባዊ ፓሪስ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
አድማ በታኝ ፖሊሶችም አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመው ከተሰበሰበው ህዝብ ጋር ግጭት ውስጥ መግባታቸው ተነግሯል።
61 ሰዎች መታሰራቸውን ተከትሎ ባለስልጣናት ቅዳሜ ምሽት በማዕከላዊ ፓሪስ ሰልፎችን ከልክለው ነበር። ቅዳሜ ምሽትም 81 ሰዎች ታስረዋል ነው የተባለው።
የፈረንሳይ የገንዘብ ሚንስትር ብሩኖ ለሜሬ ለፓሪስየን ጋዜጣ እንደተናገሩት "ማሻሻያው መተግበር አለበት። ብጥብጥን መታገስ አይቻልም" ብለዋል።
የፈረንሳይ የሰራተኛ ጥምረትን የያዘው ማህበር ለውጡን ለመቀልበስ ማስገደዱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው የማክሮን ማሻሻያ የጡረታ እድሜን በሁለት ዓመት በመጨመር ወደ 64 ያሳደገ ሲሆን፤ መንግስት እርምጃው "ስርዓቱ እንዳይበላሽ" ለማድረግ አስፈላጊ ነው ብሏል።