ከማሊና ቡርኪና ፋሶ የተባረረችው ፈረንሳይ ሌላ አፍሪካዊ ሀገር ፍለጋ ላይ መሆኗን ገለጸች
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት አዲስ የአፍሪካ ማዕከል ፍለጋ አራት ሀገራትን ሊጎበኙ ነው ተብሏል
ፕሬዝዳንቱ ሁለቱ ኮንጎዎችን ጨምሮ ጋቦን እና አንጎላን እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል
ከማሊ እና ቡርኪና ፋሶ የተባረረችው ፈረንሳይ ሌላ አፍሪካዊ ሀገር ፍለጋ ላይ መሆኗን ገለጸች።
ፈረንሳይ ጦሯን ለረጅም ዓመታት ካሰፈረችባቸው ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ጋር ያላት ግንኙነት በመበላሸቱ ሀገራቱን ለቃ መውጣቷ ይታወሳል።
በቅኝ ግዛት ዘመን ከገዛቻቸው ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየተበላሸባት ያለችው ፈረንሳይ ሌሎች ሀገራትን በማማተር ላይ ትገኛለች።
ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ የፈረንሳይ ጦር በሀገራችን አለመረጋጋት ሲሰፍን ድጋፍ አላደረገም በሚል ከሀገራቸው አስወጥተዋል።
በዚህ ምክንያትም ፈረንሳይ በአፍሪካ ለሚኖራት ማዕከል አጋር ሀገር ፍለጋ ላይ እንደሆነች በፕሬዝዳንት ማክሮን በኩል ገልጻለች።
ፕሬዝዳንቱ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ አራት ሀገራትን ለመጎብኘት ማሰባቸው ሲገለጽ ኮንጎ ብራዛቪል፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ጋቦን እና አንጎላ የሚጎበኙ ሀገራት ናቸው ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ማክሮን ወደ አራቱ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት አቅንተው በሁለትዮሽ፣ አካባቢ ጥበቃ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከመሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ተገልጿል።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከአፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ ቃል ገብተው የነበሩት ፕሬዝዳንት ማክሮን ፈረንሳይ ከማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ አልጀሪያ እና ሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት ሻክሯል።
እንዲሁም በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ፈረንሳዊያን ለዋጋ ግሽበት ተጋልጠዋል፣ ፈረንሳይ ለዩክሬን የጦር መሳሪያ ድጋፉን ያቋርጥ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የህዝብ ተቃውሞዎች እየተካሄደባቸው ይገኛል።