“ፖሊስ ህዝብ ጠባቂነቱ ቀርቶ ስርዓት ጠባቂ ከሆነ ህዝብ የሚፈልገውን አያገኝም ማለት ነው”-ሙፈሪያት ካሚል
ፖሊስ የሚመራበት አዲስ ዶክትሪን ይፋ ሆኗል
የኢትዮጵያ ፖሊስ ሊመራ የሚችልበት አዲስ “የፖሊስ ዶክትሪን እና ስታንዳርድ” ዛሬ በተካሄደ ስነ ስርዓት ይፋ ሆኗል።
ፖሊስ የሚመራበት፤ ህዝባዊ ተቋም ሆኖ የሚገነባበት መርህ ወይም ፍልስፍና ነው የተባለለት ዶክትሪኑ ከአሁን ቀደም ከፖሊስ ግልጋሎቶች ጋር በተያያዘ የሚጠቀሱ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል የታመነበት ሰነድ ነው፡፡
ሰነዱ ባለመኖሩ ምክንያት ዘመናዊና ዘመን ተሻጋሪ የፖሊስ ተቋምን ለመገንባት ሳይቻል ቀርቷል ያሉት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሠዉ ይህ በመሆኑ ምክንያት ፖሊስ በየጊዜው የሚመጡ መንግስታትን እየመሰለ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ የሚፈለገውን ዘመናዊ ተቋም ለመገንባት የማይቻል መሆኑ ታምኖበት የተለያዩ ጥናቶች ተደርገው የሃገራት ተሞክሮዎች ተወስደው ዶክትሪኑ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡
ዶክትሪኑ በግንባታ ሂደቱ የሚታዩ ችግሮችን ከመቅረፍ ባሻገር ህዝባዊ ፖሊስን ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል እንደሚታመንም ነው የገለጹት፡፡
ፖሊስ ለህብረተሰቡ ሰላም መጠበቅ የራሱን ሚና ሲጫወት ነበር የሚሉት የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው የሚመራበት የራሱ የሆነ ፍልስፍና ባለመኖሩ ከወገንተኛነት ጸድቶ ህዝብ የሚፈልገውን ግልጋሎት በተዓማመኒነት ለመስጠት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙን “ለዜጋው በቀረበ ከፓለቲካዊ ተጽዕኖ በራቀ መልኩ ስርዓት በመጣ ቁጥር ከዜሮ የማይጀምር አድርጎ መገንባት ያስፈልጋል”ም ነው ሚኒስትሯ ያሉት፡፡
ዶክትሪኑ ይህንኑ ታሳቢ አድርጎ ፓሊሳዊ አገልግሎቱን አዲስ ምዕራፍ ላይ ለማስቀመጥ በሚችል መልኩ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡
ዶክትሪኑን እና አብረውት የተዘጋጁ የማስፈጸሚያ ህጎችን በተመለከተ ገለጻዎች ተደርገዋል፡፡ በገለጻዎቹ ከፖሊሳዊ ግልጋሎቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ አቤቱታዎችን የሚሰማ ቦርድ ይቋቋማል የተባለ ሲሆን የፖሊሲ እና የአሰራር አማራጮችን የሚያቀርብ የቀድሞ የፖሊስ አባላትን የሚያሰባስብ ሃገር አቀፍ ማህበር እንደሚመሰረትም ነው የተነገረው፡፡
ከአሁን ቀደም በፖሊስ ይፈጸማሉ የሚባሉ የስቅየት ተግባራት መጣራት አለባቸው የሚሉት የዶክትሪኑ የዝግጅት ሂደት ሰብሳቢ ኮማንደር ደመላሽ ካሳዬ (ዶ/ር) ዶክትሪኑ ለፖሊስ ብቻም ሳይሆን ለህዝብ ጭምር የተዘጋጀም ነው ይላሉ፡፡
ሰብሳቢው በህዝብ ይሁንታ የሚሰራ ህዝብ የሚጠይቀው ሲፈልግ ሊያፈርሰውም የሚችል ህገ መንግስታዊ ፖሊስን ማቋቋም አለብን የሚሉም ሲሆን ተቋሙ የህዝብ እና የፖሊስ አጋርነትን ሊያጠናክር በሚችል መልኩ ከታች ወደ ላይ እንደሚገነባም ይናገራሉ፡፡
በማንነት ምክንያት ብቻ የፖሊስ አባል ከመሆን የሚቀር ኢትዮጵያዊ እንደማይኖርም ነው የሚናገሩት፡፡
ፖሊስ የሚመራበትን ፍልስፍ እና እሴቶች ማግኘቱን እንደ ጥሩ እርምጃ እንደሚወስዱት የገለጹት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) ግን ሰነዱን ማዘጋጀቱ ብቻ በቂ አይደለም ይላሉ፡፡
ተግባራዊነቱ መረጋገጥ አለበት የሚሉም ሲሆን ፖሊስ ራሱ ህግ አክባሪ ሆኖ ህግ የሚያስከብር ኃይል ሆኖ ማየትን እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ፡፡
ኮሚሽነሩ ሰነዱ የፖሊስን ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንዳለበትም ነው የሚናገሩት ጥፋተኛ የፖሊስ አባላት ሊጠየቁ የሚችሉበት ከተጽዕኖ ነጻ ስርዓት ሊኖር እንደሚገባ በመጠቆም፡፡
የፖሊስን አሰራር በገለልተኛነት የሚመረምር ተቋም መገንባት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ከአሁን ቀደም ለተስተዋሉ ችግሮች ምክንያቱ የዶክትሪን አለመኖር ነበር?
የዶክትሪኑ ዝግጅት ምን ችግር አለ ከሚለው ነው የጀመረው የሚሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ከችግሮቹ ውስጥ አንዱ የአስተሳሰብ ጉድለት ነው ይላሉ፡፡
“አዎ ችግሩ የዶክትሪን እጦትም ጭምር ነበር” የሚሉት የሰላም ሚኒስትሯ የዶክትሪን ችግር የሚሆንበት ምክንያት እሳቤ ነው ይላሉ፡፡
“ፖሊስ የሰላም ግንባታ ስራውን መስራት ያለበት በምን ዓይነት የጠራ አመለካከት ነው የሚለው የተመለሰ አይደለም” የሚሉት ሚኒስትሯ ህዝብ ጠባቂ መሆኑ ቀርቶ የስርዓት ጠባቂ ከሆነ ህዝብ የሚፈልገውን አያገኝም ማለት ነው ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
በግልጽ የሚገነባበት አስተሳሰብ ከሌለ በየወቅቱ የሚመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጡትን የግንባታ መሳሪያ የሚጠቀም ነው የሚሆነው፡፡
ይህ ደግሞ ነጻና ገለልተኛነቱን የተሟላ አያደርገውም ፡፡ ውግንና ይኖረዋል፡፡ ፖሊስን ፖሊስ የሚያደርገው ደግሞ ከውግንና መራቁ ነው እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፡፡
“ሁልጊዜ ከዜሮ የሚጀምር ሁልጊዜ እያፈረሰ የሚገነባ ሃገር ሆነን ልንቀጥል አንችልም” የሚሉት ሚኒስትሯ ዶክትሪኑ ዓመታት ሊሻገር የሚችል ዴሞክራሲን ታላሚ አድርጎ መዘጋጀቱን ያስቀምጣሉ፡፡
“ባለፉት ዓመታት ዴሞክራሲያዊ አልነበረም እናድርገው ተፈርቶ ሳይሆን ተወዶ የሚከበር እናድርገው የዛን ጊዜ ህዝብና መንግስት በጋራ ይቆማሉ ተገደው ሳይሆን ወደው” ይላሉም፡፡
ትርጓሜው ትልቅ ነው ያሉለት ዶክትሪኑ በሃገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡