በማረፍ ላይ የነበረ አውሮፕላን ባጋጠመው የእሳት አደጋ ምክንያት መንገደኞች በክንፉ ላይ ለመውጣት ተገደዱ
የአሜሪካ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን በዴንቨር አውሮፕላን ማረፍያ ሞተሩ በእሳት ተያይዟል

በአደጋው 12 ሰዎች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ
በኮሎራዶ ዴንቨር አለም አቀፍ አውሪፕላን ማረፍያ እያረፈ የሚገኝ አውሮፕላን በሞተሩ ላይ ባጋጠመው የእሳት አደጋ መንገደኖች በአውሮፕላኑ ክንፍ በኩል ወደ ውጭ ለመውጣት ተገደዋል፡፡
የአውሮፕላኑ አንደኛው ሞተር ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቁር ጭስ ወደ ሰማይ በመልቀቅ የመቀጣጠል ምልክት ማሳየቱን ተከትሎ በዋናው በር በኩል መውረድ ያልቻሉ በደርዘን የሚቆጠሩ ተጓዦች ማምለጫ አጥተው ክንፉ ላይ ቆመው ታይተዋል፡፡
የአሜሪካ አየር መንገድ ቦይንግ 737-800 ከኮሎራዶ ስፕሪንግስ ወደ ዳላስ-ፎርት ዎርዝ 172 መንገደኞች እና 6 የበረራ ሰራተኞችን ይዞ እየተጓዘ ነበር፡፡
በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 11፡15 ሲሆን የበረራ አስተናጋጆቹ በአንደኛው የአውሮፕላን ሞተር ላይ የንዝረት እና የመንቀጥቀጥ ምልክት መመልከታቸውን ተከትሎ በዴንቨር አለምአቀፍ አውሮፕላን ማርፊያ ለማረፍ መገደዱን የፌደራል አቭየሽን አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የአውሮፕላኑ አብራሪ ከማረፉ ጥቂት ቀደም ብሎ በረራው የሞተር ችግር እንዳጋጠመው ለዴንቨር የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አሳውቆ የነበረ ቢሆን ነገር ግን ሁኔታው ድንገተኛ መሆኑን እንዳልገለጸ ተሰምቷል፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያም አውሮፕላኑ እስኪያርፍ ድረስ የእሳትም ሆነ የጭስ ምልክት ባለማሳየቱ ነው፡፡
ነገር ግን አውሮፕላኑ ምድር ላይ እንዳረፈ ከፍተኛ ጭስ እና እሳት በመልቀቁ አብራሪው ለትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የአደጋ ጊዜ መልዕክት ማስተላለፉ ተነግሯል፡፡
ይህን ተከትሎም በሞተሩ አቅራቢያ የሚገኘውን የአውሮፕላን በር መክፈት ባለመቻሉ አንዳንድ መንገደኞች በአውሮፕላኑ እቃ መጫኛ ክፍል በኩል በመንሸራተቻ ሲወርዱ ሌሎች ደግሞ ክንፉ ላይ ቆመው ታይተዋል፡፡
በአደጋው 12 መንገደኞች ካጋጠማቸው መጠነኛ ጉዳት ባለፈ በንብረት እና በሰው ላይ የከፋ ጉዳት አለመፈጠሩ ተሰምቷል፡፡
የአሜሪካ አየር መንገድ ወደ ዴንቨር ተቀያሪ አውሮፕላን በመላክ መንገደኞቹ የዳላስ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡
የትላንቱ የአውሮፕላን ሞተር እሳት የዴልታ አየር መንገድ በቶሮንቶ ፒርሰን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማኮብኮቢያ ላይ ተገልብጦ በእሳት ከተያያዘ ከሶስት ሳምንታት በኋላ የተከሰተ ነው።
ከሁለቱ አደጋዎች ቀደም ብሎ በአላስካ ፣ ፊላዴልፊያ እና ዋሽንግተን ዲሲ የሰው ህይወት ጭምር ያለፈባቸው አደጋዎች ተመዝግበዋል፡፡
በሌላ በኩል በታህሳስ ወር በደቡብ ኮሪያ እና በካዛኪስታን የደረሱ የአውሮፕላን አደጋዎች ከ200 በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፈዋል።