አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከ20 በላይ ሀገራት በትግራይ ክልል ያለው አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው ገለጹ
ለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቆም ምክንያት የሆነው ስምምነት እንዲከበርም ሀገራቱ ጠይቀዋል

ሀገራቱ በክልሉ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በውይይት ሊፈቱ ይገባልም ብለዋል
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከ20 በላይ ሀገራት በትግራይ ክልል ያለው አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው ገለጹ፡፡
በትግራይ ክልል በጊዜያዊ አስተዳድሩ እና በእነ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ቡድን መካከል ግጭት መከሰቱን ተከትሎ የመፈንቅለ መንግስት እየተፈጸመ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳድር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳ በመቀሌ እና አዲ አበባ በሰጧቸው መግለጫዎች ላይ እንዳሉት የህወሃት አንዱ ክንፍ በጊዜያዊ አስተዳድሩ ላይ አመራሮችን መሾም፣ ማህተም መቀማት፣ ቢሮዎችን መቆጣጠር እና ሌሎች ህጋዊ ያልሆኑ ስራዎችን እያካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በትግራይ ክልል አለመረጋጋት የተፈጠረ ሲሆን በክልሉ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚሉ ስጋቶች አይለዋል፡፡
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ከ20 በላይ ሀገራትም በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ ገልጸዋል፡፡
የጋራ መግለጫውን ካወጡ ሀገራት መካከል አሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ጀርመን፣ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ቤልጂየም እና ሌሎችም ሀገራት ይገኙበታል፡፡
ሀገራቱ በጋራ መግለጫቸው ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ለነበረው ጦርነት መቆም ምክንያት የሆነው የሰላም ስምምነት ሊጣስ እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ ጦርነትን ያስቆመ መሆኑን የተናገሩት ሀገራቱ ወደ ግጭት የገቡ አካላት ልዩነቶቻቸውን በስምምነት እንዲፈቱም አሳስበዋል፡፡
ወደ ግጭት ያመሩ አካላት ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ሀገራቱ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ መዲና ፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ከ1 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር በላይ የቁስ ውድመት ማድረሱ ይታወሳል፡፡
እንዲሁም በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ደግም ለመመለስ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የገንዘብ ሚኒስቴር በጦርነት ውድመት ሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡