ትራምፕ ኑክሌር ከታጠቀችው ሰሜን ኮሪያ መሪ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ አሉ
ሰሜን ኮሪያ ትራምፕ ወደ ኋይትሀውስ ከገቡ በኋሃ ለመጀመረያ ጊዜ በርካታ የባለስቲክ ሚሳይሎችን አስወንጭፋለች

ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው የኪም እህት ኪም ዮ ጆንግ የትራምፕ አስተዳደርን ትንኮሳ አጠናክሯል በሚል ከሰዋል
ትራምፕ ኑክሌር ከታጠቀችው ሰሜን ኮሪያ መሪ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ አሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ወቅት በርካታ ስብሰባዎች ካደረጉት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ትራምፕ በኃይትሀውስ ከኔቶ ዋና ጸኃፊ ጋር ማርክ ሩቴ ጋር በነበራቸው ስብሰባ ወቅት ከኪም ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እቅድ እንዳላቸው ተጠይቀው " ከኪም ጆንግ ኡን ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ፤ የሚሆነውን እናያለን። ነገርግን በእርግጠኝነት ኑክሌር አለው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸው ባለፈው ጥር ወር በዓለ ሲመታቸውን በፈጸሙበት ወቅት ሰሜን ኮሪያ "ኑክሌር የታጠቀች" ነች ማለታቸው ሀገሪቱ የኑክሌር ትጥቋን እንድትፈታ ከማድረግ(ዲኑክሌራይዜሽን) ይልቅ የጦር መሳሪያ ቅነሳ ንግግር ላይ ሊተኩሩ ይችላሉ የሚል ጥያቄ ፈጥሮ ነበር።
የሩሲያና ቻይናን የኑክሌር መሳሪያ በተመለከተ ትራምፕ "ቁጥሩን መቀነስ ከቻልን ትልቅ ስኬት ነው። ብዙ መሳሪያ አለን፤ ኃይሉም ጥሩ ነው" ብለዋል።
ትራምፕ ኪም ብቻ ሳይሆን ህንድ፣ ፓኪስታንና ሌሎችም የኑክሌር ጦር መሳሪያ ስላላቸው እነሱም በቅነሳ ንግግሩ ላይ እንዲካተቱ እንፈልጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
ትራምፕ የሰጡት አስተያየት አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ትከተለው የነበረው ፖሊሲ መቀየሩን የሚያሳይ እንደሆነ የተጠየቁት የኃይትሀውስ ባለስልጣን "ፕሬዝደንት ትራምፕ በመጀመሪያ የሰልጣን ዘመናቸው ወቅት እንዳደረጉት ሁሉ ሰሜን ኮሪያ ሙሉ በሙሉ የኑክሌር ትጥቋን እንድትፈታ ይፈልጋሉ" ብለዋል።
ባለፈው የካቲት ወር የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮና የጃፓን እና የደቡብ ኮሪያ አቻዎቻቸው ሰሜን ኮሪያ በተመድ የጸጥታው ምክርቤት ውሳኔ መሰረት የኑክሌር ትጥቋን እንድትፈታ እንደሚፈልጉ ገልጽ አድርገዋል።
ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ ስልጣን ያላቸው የኪም እህት ኪም ዮ ጆንግ የትራምፕ አስተዳደርን ትንኮሳ አጠናክሯል በሚል ከሰውታል። በዚህ ሳምንት ደግሞ ሰሜን ኮሪያ ትራምፕ ወደ ኋይትሀውስ ከገቡ በኋሃ ለመጀመረያ ጊዜ በርካታ የባለስቲክ ሚሳይሎችን አስወንጭፋለች።