ፕሬዝዳንቱ ከጋዳፊ ከስልጣን መወገድ በኋላ ወደ ሊቢያ ያቀኑ የመጀመሪያው የቱኒዚያ መሪ ናቸው
የቱኒዚያው ፕሬዝዳንት ካይስ ሰዒድ ለይፋዊ ጉብኝት ዛሬ ሊቢያ ገቡ፡፡
ካይስ ከ2012 ወዲህ ወደ ሊቢያ ያቀኑ የመጀመሪያው የቱኒዚያ መሪ ናቸው ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ትሪፖሊ ሚቲጋ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱ ጊዜ በፕሬዝዳንታዊ ምር ቤት መሪው መሃመድ መንፊ እና በምክትላቸው አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
ከሙዓመር ጋዳፊ ከስልጣን መወገድ ወዲህ በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ያሳለፈችው ሊቢያ ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትር አብዱል ሃሚድ ዲቤባ የሚመራ ጊዜያዊ የአንድነት መንግስትን መስርታለች፡፡
ዲቤባ የተከፋፈለችውን ሊቢያን ወደ አንድ በማምጣት በመጪው ዓመት ወርሃ ታህሳስ ሃር አቀፍ ምርጫ ለማድረግ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ካይስ በሊቢያውያን ዘንድ ትልቅ ተስፋ የፈነጠቀውን ይህን አጋጣሚ ለመደገፍ እና የሃገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በማሰብ ወደ ትሪፖሊ ማቅናታቸውንም ነው ጽህፈት ቤታቸው ያስታወቀው፡፡
ቱኒዚያ የግብርና ምርቶችን ወደ ሊቢያ ትልክ ነበር፡፡ በርካታ ዜጎቿም በነዳጅ በበለጸገችው ሊቢያ ይሰሩና ይኖሩ እንደነበርም ይነገራል፡፡
የህግ ምሁሩ ካይስ እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ ቱኒዚያን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ መሆናቸው የሚታወስ ነው፡፡