ፓትሪክ ቪዬራ የክሪስታል ፓላስ አሠልጣኝ ሆኖ ተሾመ
ቪዬራ እ.ኤ.አ በ2010 ማንችስተር ሲቲን ተቀላቅሎ ከክለቡ ጋር የኤፍ ኤ ዋንጫን ካነሳ በኋላ ጫማ መስቀሉን አይዘነጋም
ቪዬራ "ይህን ዕድል አግኝቼ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ በመመለሴ እጅግ ደስተኛ ነኝ" ብሏል
ክሪስታል ፓላስ የቀድመውን የአርሰናል አምበል ፓትሪክ ቪዬራን አሠልጣኝ አድርጎ መቅጠሩን ይፋ አደረገ።
ቪዬራ፤ ሮይ ሆጅሰንን ተክቶ ነው የፓላስ አሠልጣኝ ሆኖ የተሾመው።
የ45 ዓመቱ ፈረንሳዊ ባለፈው የውድድር ዘመን 14ኛ ሆነው ካጠናቀቁት ፓላሶች ጋር ለሶስት ዓመታት የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።
ቪዬራ "ይህን ዕድል አግኝቼ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ በመመለሴ እጅግ ደስተኛ ነኝ" ብሏል፡፡
"ለኔ በጣም ትልቅ ቦታ የምሰጠው ፕሮጀክት ነው። ከክለቡ አለቃና ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ጋር ክለቡ ስላለው ዓላማ ብዙ አውርተናል"ም ነው ያለው ቪዬራ።
ክለቡ በፕሪሚዬር ሊጉ በርካታ ዓመታትን የዘለቀ እንደመሆኑ ይህን ተንተርሰን ክለቡን ወደ ተሻለ ቦታ ለመውሰድ ተስፋ እንዳለውም ጭምር፡፡
ቪዬራ ከፈረንሳዩ ክለብ ኒስ አሠልጣኝነት የተባረረው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ነበር።
ከዚያ በፊት በአሜሪካው ሱፐር ሊግ ሶከር የሚጫወተው ኒው ዮርክ ሲቲ አሠልጣኝ ሆኖ ለሁለት ዓመት ተኩል አገልግሏል።
ቪዬራ የአሠልጣኝነት ዘመኑን የጀመረው በማንቸስተር ሲቲ አካዳሚ ሲሆን የተጫዋችነት ዘመኑንም የቋጨው በሲቲ ነው።
ከኒስ ጋር በነበረው ቆይታ በአንደኛው ዓመት ሰባተኛ በሁለተኛው ደግሞ አምስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሎ ነበር።
ለአራት ዓመታት ከፓላስ ጋር የቆዩት የ73 ዓመቱ ሮይ ሆጅሰን በጎልማሳው ቪዬራ ተተክተዋል።
ፈረንሳዊው አማካይ ቪዬራ ከአርሰናል ጋር በፈረንጆቹ ከ1996 እስከ 2005 በነበረው ቆይታ 9 ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።
ከፈረንሳይ ጋር የዓለምና የአውሮፓ ዋንጫን ማንሳት የቻለው ቪዬራ ከኢንተር ሚላን ጋርም ሶስት የሴሪ ኤ ዋንጫዎችን በልቷል።
ቪዬራ ማንችስተር ሲቲን የተቀላቀለው በፈረንጆቹ 2010 ሲሆን ከክለቡ ጋር የኤፍ ኤ ዋንጫን ካነሳ በኋላ ጫማ መስቀሉን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።