ሦስቱ የትግራይ ክልል ክለቦች በ2014 ፕሪሚየር ሊግ መሳተፍ እንደሚፈልጉ ተገለጸ
ክለቦቹ ወደ ውድድር ለመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም የበጀት ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከክለቦቹ ጋር ስለ ቀጣይ የውድድር ዘመን ተሳትፏቸው ተወያይቷል
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሦስቱ የትግራይ ክልል የፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የነበሩ ክለቦች (መቐለ 70 አንደርታ ፣ ስሁል ሽረ እና ወልዋሎ አዲግራት) ጋር ስለ ቀጣይ የውድድር ዘመን ተሳትፏቸው በተመለከተ በአዲስ አበባ ተወያይቷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ አበበ ገላጋይ እና የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሀፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን ከክለቦቹ እና ከክልሉ ስፖርት ኮሚሽን ጋር ተነጋግረዋል።
በውይይቱ ላይ የመቐለ 70 እንደርታ፣ የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ፣ የትግራይ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የትግራይ ክልል ስፖርት ኮሚሽን አመራሮች በአካል በመገኘት ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም የስሁል ሽረ አመራሮች በአካል መገኘት ባለመቻላቸው በቀጥታ የቴሌ ኮንፈረንስ በውይይቱ ላይ መሳተፋቸውን ፌዴሬሽኑ በድረገጹ አስታውቋል።
ክለቦቹ በውይይቱ ላይ በአሁን ወቅት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ አስረድተው ወደ ውድድር ለመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም የበጀት ችግር እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ክለቦቹ ከውይይቱ በኋላ ከደጋፊዎቻቸው እና ከክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ጋር በመነጋገር በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔያቸውን እንደሚያሳውቁ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በፌደራል ስፖርት ኮሚሽን በኩል ለትግራይ ክልል ድጋፍ ማድረጉን እና ክለቦቹ ወደ ውድድር እንዲመለሱም ለማድረግ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጿል።