በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 29 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 29 መድረሱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
በቫይረሱ ተያዙት ሶስት ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያውያ ሲሆኑ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በ24 ሰአት ውስጥ 68 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አካሂዶ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው በቫይረሱ የተያዙት የ33፣የ26ና የ32 እድሜ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት ህክምና እየተደረገላቸው ያሉ 25 ታማሚዎች ሲሆን ሁለት ታማሚዎች ደግሞ ሙሉበሙሉ ማገገማቸውን ሚኒስቴሩ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡
መንግስት የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፤ እየወሰደም ይገኛል፡፡
ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ፣ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ እንዲሆኑና እንዲሁም ብዙ ህዝብ የሚሳተፍባቸው ስብሰባዎችም እንዲሰረዙ መንግስት ቀደም ብሎ ወስኖ ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መንግስት የዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ በማሰብ የመንግስት መስሪያቤቶች እንዲዘጉና የኢትዮጵያ ድንበሮች ለሰዎች ዝውውር ዝግ እንዲሆኑ መወሰኑም የሚታወስ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የክልል መንግስታትም የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
የትግራይ ክልል “የአስቸኳይ ጊዜ” አዋጅ በማወጅ ሰዎች ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ እንዳይንቀሳቀሱ እግድ የጣለ ሲሆን የአማራ ክልል ደግሞ ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ክልሉ የሚገቡ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደማይኖሩ በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ የደቡብ ክልልም አዲስ አበባን ጨምሮ ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የሚደረጉ የህዝብ ትራንስፖርስት ስምሪት እንቋረጥ ወስኗል፡፡
ከሶስት ቀናት በፊት ደግሞ የኦሮሚያ ክልልም የህዝብ እንቅስቃሴን የሚገድብ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መጋቢት 4፣ 2012 የተከሰተ ሲሆን አሁን ላይ በኦሮሚያና በአማራ ክልልና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መገኘቱ ተረጋግጧል፡፡