ዛሬ በአማራ ክልል የተገኙ ሁለት (2) የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተጠቂዎች ቁጥር 23 ደርሷል
ዛሬ በአማራ ክልል የተገኙ ሁለት (2) የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተጠቂዎች ቁጥር 23 ደርሷል
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ባደረገው ተጨማሪ ስልሳ ስድስት (66) የላብራቶሪ ምርመራ ሁለት (2) በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች በማረጋገጡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሃያ ሶስት (23) ደርሷል፡፡
በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ግለሰቦች በአማራ ክልል ባህር ዳር ነዋሪ የሆኑ የ37 ዓመት ሴትና በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የአዲስ ቅዳም ነዋሪ የሆኑ የ32 ዓመት ወንድ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ከመጀመሩ ዕለት አስቀድሞ አንደኛዋ ታማሚ መጋቢት 10 ከዱባይ እንዲሁም ሁለተኛው ታማሚ መጋቢት 12 ከአሜሪካ የገቡ ናቸው፡፡
ሁለቱም ታማሚዎች የበሽታው ምልክት በማሳየታቸው በላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዘቸው ተረጋግጧል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከታማሚዎቹ ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመለየትና የመከታተል ሂደት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ሁለቱም ታማሚዎች በአማራ ክልል የለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ አስራ ዘጠኝ (19) ታማሚዎች ሲኖሩ አንድ ታማሚ በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላት ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ሁለት ታማሚዎች ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ፡፡ ሁለት ታማሚዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገግመዋል፡፡ ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ቫይረሱ ከአዲስ አበባ ውጭ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ተገኝቷል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በፌደራል መንግስት እየተወሰዱ ከሚገኙ እርምጃዎች በተጨማሪ ክልሎችም የየራሳቸውን እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል፡፡
የትግራይ ክልል “የአስቸኳይ ጊዜ” አዋጅ በማወጅ ሰዎች ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ የጣለ ሲሆን የአማራ እና የደቡብ ክልሎች ደግሞ ከሁሉም አቅጣጫ ወደየክልሎቹ የሚገቡ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደማይኖሩ በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የአዳማ እና የአሰላ ከተማ አስተዳደሮችም የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ተወስኗል፡፡