በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 23 ገደማ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታወቁ
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 23 ገደማ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስታወቁ
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 23 ገደማ መድረሱን የሚያሳይ ሪፖርት ዛሬ እንደደረሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
እስካሁን ከተመረመሩት 800 ሰዎች ውስጥ 23 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያሳይ ሪፖርት እንደደረሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚስኒትር ዐቢይ ማህበረሰቡ ርቀቱን በመጠበቅና ራሱን በማሸነፍ ከቫይረሱ ራሱን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል፤ እየወሰደም ይገኛል፡፡
ትምህርት ቤቶች ዝግ ሆነው እንዲቆዩ፣ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ እንዲሆኑና እንዲሁም ብዙ ህዝብ የሚሳተፍባቸው ስብሰባዎችም እንዲሰረዙ መንግስት ቀደም ብሎ ወስኖ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መንግስት የዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ በማሰብ የመንግስት መስሪያቤቶች እንዲዘጉና የኢትዮጵያ ድንበሮች ለሰዎች ዝውውር ዝግ እንዲሆኑ መወሰኑም የሚታወስ ነው፡፡
ከፌደራል መንግስት ውሳኔዎች ጎን ለጎን የክልል መንግስታት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እያሳለፉ ይገኛሉ፡፡
የትግራይ ክልል “የአስቸኳይ ጊዜ” አዋጅ በማወጅ ሰዎች ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ እንዳይንቀሳቀሱ እግድ የጣለ ሲሆን የአማራ ክልል ደግሞ ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ክልሉ የሚገቡ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንደማይኖሩ በትናንትናው እለት አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ የደቡብ ክልል ከዛሬ 6 ሰዓት ጀምሮ አዲስ አበባን ጨምሮ ከሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች የሚደረጉ የህዝብ ትራንስፖርስት ስምሪት እንቋረጥ ወስኗል፡፡
ቫይረሱ ከአዲስ አበባ ውጭ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ ተመዝግቧል፡፡
ቫይረሱ አዲስ አበባ ውስጥ መገኘቱ ሪፖርት ከተደረገበት መጋቢት 4፣ 2012ዓ.ም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር አረጋግጧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስካሁን 34,034 ለሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን የወርልዶሜትር መረጃ ያሳያል፡፡ እንደወርልዶሜትር መረጃ ከሆነ እስካሁን 725,230 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 152,185 ሰዎች አገግመው ከቫይረሱ ነፃ ሆነዋል፡፡