ከህዳሴ ግድቡ ጋር ተያይዞ በዘንድሮው ክረምት “የደረሰብኝ የጎርፍ አደጋ የለም”- ሱዳን
አባስ የነጭ ዓባይ የውሃ መጠን ለባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍ ማለቱንም ነው የተናገሩት
ፕ/ር ያሲር አባስ ኢትዮጵያ ግድብ እየገነባች ካለችበት የዓባይ ውሃ ይልቅ ዘንድሮ ነጭ ዓባይ ሱዳንን ለጎርፍ አደጋ አጋልጧታል ብለዋል
የሱዳን የመስኖ እና ውሃ ሃብት ሚኒስትር ያሲር አባስ (ፕ/ር) ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ያጋጠማት የጎርፍ አደጋ እንደሌለ አስታወቁ፡፡
ፕ/ር ያሲር አባስ ኢትዮጵያ ግድብ እየገነባች ካለችበት የዓባይ ውሃ ይልቅ ዘንድሮ ነጭ ዓባይ ሱዳንን ለጎርፍ አደጋ አጋልጧታል ብለዋል፡፡
ይህ ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት ታይቶ አይታወቅምም ነው አባስ ያሉት፡፡
ክረምት በመጣ ጊዜ በቀን ወደ ሱዳን ይገባ የነበረው ከ70 እስከ 80 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መጠን ያለው የነጭ ዓባይ ውሃ ዘንድሮ በቀን ከ120-130 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል።
ሆኖም በተያዘው ክረምት ሊያጋጥም ይችል የነበረውን የጎርፍ አደጋ በሮዜሪዬስ እና ሜሮዔ ግድቦች የተያዘውን ውሃ በአግባቡ በመልቀቅ ለመቆጣጠር መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡን ሁለተኛ ዙር ሙሌት በተናጠል ከማከናወኗ ውጭ ክረምቱን ተከትሎ በሱዳን ካጋጠሙ የጎርፍ አደጋዎች ጋር የተያያዘ ተጽዕኖ እንደሌለውም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ከሙሌቱ በፊት መረጃን በወጉ ለመለዋወጥ አለመቻሉ ለቅድመ መከላከል ተግባራት ከፍተኛ ወጪ፣ ለተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊ እና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች ዳርጎናልም ነው ፕ/ር ያሲር አባስ ያሉት፡፡
አባስ አል ፋው እና አል-ራሃድ በተሰኙ ከተሞች በእርሻ መሬቶች ጭምር የደረሰውን የጎርፍ አደጋ በተመለከተ የቀረቡ ሪፖርቶችን ገምግመናል፤ ተወያይተናልም ብለዋል፡፡
ሱዳን ከሙሌቱ በፊት የመረጃ ልውውጥ አልነበረም ትበል እንጂ ኢትዮጵያ ግን ሙሌቱን የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎችን ልኬያለሁ ስትል ከአሁን ቀደም ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡