በሁለቱ የጉራጌ ዞኖች ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ግጭቶች እያጋጠሙ መሆናቸውን ጎጎት ገለጸ
ከመጋቢት 21 እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም ሕፃናትን ጨምሮ 44 ሰዎች መገደላቸው ፓርቲው ገልጿል
ጎጎት መንግስት በተገቢው ጊዜ የአስተዳደር ወሰን ጥያቄዎች ላይ እልባት አለመስጠቱ ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግሮችን እያሰከተለ ነው ብሏል
በጉራጌ እና ምስራቅ ጉራጌ ዞኖች ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ግጭቶች እያጋጠሙ መሆናቸውን ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) ገለጸ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በሚገኙት ሁለቱ የጉራጌ ዞኖች ከወሰን ማስከበር እና ከሌሎች የጸጥታ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የሰላም መደፍረስ ለሰዎች ሞት ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ ጎጎት ለአል ዐይን አማረኛ ተናግሯል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ጀሚል ሳኒ ከመጋቢት 21 እስከ ነሐሴ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕፃናትን ጨምሮ 32 ወንዶችና 12 ሴቶች በጠቅላላው 44 ሰዎች መገደላቸውን፣ ከ6,000 ሺህ በላይ የሚሆኑት መፈናቀላቸውንና 36 ሰዎችም በእስር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ሀላፊው እንደሚሉት አዲስ በተዋቀረው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጸጥታ ችግር ካለባቸው አካባቢዎች ውስጥ አምስቱ በሁለቱ የጎራጌ ዞኖች የሚገኙ ናቸው፡፡
ከ2008 ጀምሮ ተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትበት የመስቃን እና ማረቆ የይዞታ ይገባኛል ቅራኔ፣ በወልቂጤ ከተማ ዙርያ በቀቤና ልዩ ወረዳ እና በጎራጌዞን መካከል የሚገኝው ውዝግብ፤
እንዲሁም ባለፉት አመታት “ቆስየ” ተብላ የምትጠራው አካባቢ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ በኢመደበኛ አስተዳደር መተዳዳር መጀመሩ ለክልሉ ሰላም እና ጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ከሆኑ ዋና ዋና ምክንያቶች መካል እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በሶዶ እና ደቡብ ሶዶ ታጣቂ ሀይሎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ እገታ ፣ ዝርፍያ እና የሰዎች ግድያ እየተበራከተ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
የህዝብ ግንኙነት ሀላፊው አቶ ጀሚል ሲናገሩ “ሶስት ቀበሌዎችን ይዞ በሚገኝው ቆስየ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ ከወጣ አምስት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ስፍራ መንግስት ሁነኛ የህግ ማስከበር ስራን በመስራት የአባቢውን ደህንነት ከማስከበር ይልቅ በተደጋጋሚ በእርቅ ስሚ የሚያደርጋቸው ውይይቶች ውጤት አላመጡም” ብለዋል፡፡
ኢመደበኛ የተባሉት ሀይሎች ይህንን ለማስቆም የሚሞክሩ ሰዎችን በምሽት ተደራጅተው በመምጣት ጥቃት እንደሚፈጽሙም የሚናገሩት ሀላፊው ችግሩ በክልል ምክር ቤት ደረጃ ድረስ የሚታወቅ ቢሆንም አሁንም መፍትሄ እንዳልተገኝለት ነው የተናገሩት፡፡
በሁለቱ የሶዶ ወረዳዎች ለሚፈጠሩ ችግሮች በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መንግስት "ሸኔ ብሎ" በሽብርተኝነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና በአማራ ክልል ከመንግስት ሀይሎች ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኙት የፋኖ አባላትን የጉራጌ ዞን አስተዳዳር ተጠያቂ ናቸው ሲል ይከሳል፡፡
ጎጎት በነዚህ ወረዳዎች መንግስት አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ የሚቸገር ከሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ እራሱን የሚከላከልበት መንገድ ሊመቻችለት እንደሚገባ ይናገራል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው እንደሚሉት “ይህ አካባቢ ተደጋጋሚ ጥቃት እና እገታ የሚፈጸመብት ነው፤ አሁን ባለው የሀገሪቱ ሁኔታ መንግስት ሁሉም አካባቢዎች ላይ ሰራዊት መመደብ ስለማይችል የአካባቢው ወጣቶች እንዲሰልጥኑ እና እንዲደራጁ አካባቢያቸውንም እንዲጠብቁ ሊደረግ ይገባል”፡፡
በአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና ገዳማውያን ጭምር የእገታ ሰላባ ሆነዋል የተባለ ሲሆን ከ16 በላይ የታገቱ ገበሬዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና ነዋሪዎችን ለማስለቀቅ ከ2.9 ሚሊዮን ብር በላይ መከፈሉ ተነግሯል፡፡
የመስቃን እና የማረቆን ግጭት በተመለከተ ከ8 አመታት በላይ አስቆጥሯል። በተደጋጋሚ ግጭት የሚከሰትበት አካባቢ ሲሆን በአሁኑ ወቅት አካባቢው በኮማንድ ፖስት እየተዳደረ እንደሚገኝ ሰምተናል፡፡
ሌላኛው ችግር በጉራጌ ዞን ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ጋር በተገናኘ ያለው ውዝግብ ነው።
የጎጎት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ እንደሚሉት ከ2016 ጥቅምት ወር በኋላ አዲሱ አወቃቀር ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በከተማዋ ይገባኛል ጥያቄ የአስተዳዳር ችግር መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡
“በአዲሱ የክልል እና የዞን አወቃቀር ወልቂጤ የጉራጌ ዞን መቀመጫ እንደሆነች ቢቀመጥም አዲስ የተዋቀረው የቀቤና ልዩ ወረዳ በከተማዋ ላይ ይገባኛል ጥያቄ አንስቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም የቀቤና ልዩ ወረዳ በወልቂጤ ከተማ ፖሊስ እና ትራፊኮችን ማሰማራት ፣ ወደ ወልቂጤ ከተማ አስተዳደሩን ለማዞር እና ግብር የመሰብሰብ እንቅስቃሴ እንዳለም እየታዘብን ነው፤ ይህ ደግሞ እየሰፋ ከመጣ የከተማዋ በአጠቃላይ የዞኑ አስተዳደራዊ መዋቅርም ላይ ችግር የሚስከትል መሆኑን መገንዘብ ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የተጠቀሱት ችግሮች የክልሉ መንግስት እና የዞኖቹ መራሮች አስፈላጊውን የወሰን ማስከበር እና ማካለል ስራዎችን በመስራት ህግን ማስከበር ቢጠበቅባቸውም ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ እያደረጉ አይደሉም ሲል ጎጎት ወቅሷል፡፡
በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉ ችግሮች በዝምታ መታለፋቸው የዞንኑ አጠቃላይ የሰላም ሁኔታ አደጋ ውስጥ እየከተቱ ይገኛሉ ያሉት አቶ ጀሚል የፌደራል መንግስት የክልል እና የዞን አስተዳዳሪዎች አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያበጁ ጠይቀዋል፡፡
አል ዐይን ዐማረኛ በጉዳዩ ዙርያ ምላሽ የጠየቃቸው የጎራጌ ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምርያ ሀላፊ አቶ ያህያ ሱልጣን ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ ያነሳቸውን የጸጥታ ችግሮች መኖራቸውን አምነው በተለይ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ የሚነሱት ችግርች ዞኑ በአዲስ ከመዋቀሩ በፊት የነበሩ ናቸው ብለዋል፡፡
ከወልቄጢ ከተማ ጋር በተያያዘ የሚነሱ የይገባኛል ጥያቄዎችን መፍትሄ ለማበጀት ከፌደራል ከክልል እና ከዞን የተውጣጡ የመንግስት ሃላፊዎች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በዚህ አካባቢ የሚገኙ ችግሮች አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንደሚፈልጉ የሚናገሩት የጸጥታ መምሪያ ሀላፊው በሰላም እና ጸጥታ ዙርያ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ቢሯቸው እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ቆስየ የተባለው አካባቢ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ “አዚህ አካባቢ ላይ የመልካም አስተዳር እና የመሰረተ ልማት አለብን የሚሉ አካላት ባነሱት ጥያቄ መነሻ እራሳችንን እናስተዳድራለን ወደሚል አካሄድ ገብተዋል፡፡
በአካባቢው በተደጋጋሚ የሰላም ኮንፈረንሶችን በማካሄድ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ቢደረግም የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው አካላት ህዝቡን በማነሳሳት ከመንግስት አስተዳደር ቁጥጥር ውጪ እንዲወጣ አድረገውታል” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዞኑ የተፈናቀሉ ሰዎችን እና ቀደም ብሎ የነበረውን አስተዳደር ወደ ስፍራቸው ለመመለስ እና ኢመደበኛ የተባሉትን አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ሃላፊው ይህን ቢሉም አሁንም ሶስት ቀበሌዎች ከመንግስት አስተዳደር ውጪ እንደሚገኙ አልሸሸጉም፡፡
የጎራጌ ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምርያ ሀላፊ አቶ ያህያ ሱልጣን “በርከት የሚሉት ጥያቄዎች ከአስተዳደር ወሰን ጋር የሚገናኙ ናቸው ይህን ለመቅረፍ ክልሉ እና ዞኑ በአዲስ የተዋቀረበትን መንገድ መነሻ በማድረግ መፍትሄ መስጠት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ቦታዎችን ደግሞ በድርድር እና በፖለቲካ ውሳኔዎች የሚፈቱ ናቸው”፡፡
በተጨማሪም “እስካሁን በእርቅና በሽምግልና ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት አድርገናል ከዚህ በኋላ ግን የፌደራል የክልል እና የዞኑ አስተዳደር በሚሰጡት መመሪያ ጠንካራ የህግ ማስከበር ስራዎችን ለመስራት እየተዘጋጀን ነው የምንገኝው” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፡፡