ከጉራጌ የክልል ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተፈፀመው እስር ፖለቲካዊ መሆኑን ጠበቆቻቸው ተናገሩ
ጎጎት ፓርቲ የጉራጌ ህዝብ ለህገ-መንግስታዊ መብቱ "መስዋዕት እየከፈለ ነው ብላል
በጉራጌ ዞን የታወጀው ኮማንድ ፖስት እንዲነሳና እስረኞች እንዲፈቱ ተጠይቋል
ከጉራጌ ዞን የክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ 50 የሚሆኑ ሰዎች በጅምላ መታሰራቸው ተነግራል።
ንቁ ተሳትፎ ያላቸው ዜጎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ የሚዲያ ባለሞያዎች፣ የህግ ባለሞያዎችና የምክር ቤት አባላት ወልቂጤና ቡታጅታ ታስረው እንደሚገኙ ጠበቆች ተናግረዋል።
እስራቸው ጉራጌ ክልል እዲሆን በሚደርገው እንቅስቃሴ ኢላማ ተደርገው መሆኑን የሚናገሩት ጠበቆች፤ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታቸው እንደተገፈፈ አንስተዋል፡፡
ያለመከሰስ መብት ያላቸው የምክር ቤት አባላትም መታሰራቸው ታውቋል።
እስረኞቹን መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድና የሽብር ቡድን ለማቋቋም በመሰሉ ወንጀሎች እንደጠረጠራቸው ፖሊስ ለፍርድ ቤት አሳውቃል፡፡
አስር ለሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ጥብቅና የቆሙት ጠበቃና የህግ አማካሪው ቶፈቅ በድሉ፤ “እስሩ ፖለቲካዊ ነው” ብለዋል።
"በህግ አግባብ ፍ/ቤትም እየቀረቡ አይደለም፤ ታሳሪዎቹ እስር ቤት እንዲማቅቁ፣ ዲሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ መብታቸው እንዲጣስ እየተደረገ ነው፤ምክንያቱም መቶ በመቶ ማለት ይቻላል ታሳሪዎቹ ጉራጌ በክላስተር እንዲደራጅ የማይፈልጉ ወይም የክልል ጥያቄ የሚድፉ በመሆናቸው ነው ብለዋል።
“መንግስት ያቀረበውን የክላስተር ሀሳብ የተቃወሙ ናቸው ተነጥለው የታሰሩት” ያሉት ጠበቃው፤ “ስለዚህ እስሩ የፖለቲካ አፈና ነው እንጂ ህጋዊ እስር አይደለም፤የፈጸሙት ምንም አይነት ወንጀልም የለም" ብለዋል።
ከ20 በላይ የሚሆኑ ጠበቆች በቡድን ለተጠርጣሪዎች ጥብቅና መቆማቸውን አል ዐይን ሰምቷል።
ዞኑ ከህዳር አጋማሽ ጀምሮ በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሲሆን፤ የህግ ባለሞያዎች ኮማንድ ፖስቱ በም/ቤት አልታወጀም በሚል ህጋዊነቱ ላይ ጥያቄ ከማንሳት ባለፈ "የጸጥታ ኃይሎች ጅምላ እስር ለመፈጸም እየተጠቀሙበት ነው" ሲሉም ከሰዋል።
በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ለጉራጌ ህዝብ ለመታገል ተመስርቻለሁ ሲል ምስረታውን ያበሰረው ጎጎት ለጉራጌ አንድነትና ፍትህ ፓርቲ (ጎጎት) በዚህ ሀሳብ ይስማማል።
የፓርቲው ሊቀ-መንበር መሀመድ አብራር ለከል ዐይን ጋ በነበራው ቆይታ፤ የጉራጌ ህዝብ የክልል ልሁን ጥያቄ ካነሳ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ መብቱ እየተገፈፈ ነው ይላሉ።
በተለይም ከ2012 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የደቡብ ክልል መንግስት ያወጣቸውን አደረጃጀቶች በመቃዎሙ መራር ዋጋ እየከፈለ ነው ብለዋል።
የጉራጌን ክልል የመሆን ጥያቄ የደገፉ የም/ቤት አባላትና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ሳይቀር ከስራ እየታገዱና እየታሰሩ ነው ያሉት ሊቀ-መንበሩ፤ በዞኑ እስርና አፈና እየተፈጸመ ነው ብለዋል።
ዞኑ ራሱን በራሱ የማስተዳደርና የመሰረተ-ልማት ችግር ስላለበት የክልል ጥያቄ ማንሳቱን የሚናገሩት የጎጎት ሊቀ-መንበር፤ ሆኖም ይህ መብት ከህገ-መንግስታዊ መብት ይልቅ "በመንግስት አመራሮች ችሮታ" ላይ መውደቁን አንስተዋል፡፡
መንግስት ህገ-መንግስታዊ መብትን እንዲያስከብር፣ ኮማንድ ፖስቱን እንዲያነሳና እስረኞችን እንዲፈታ ጎጎት ጠይቋል፡፡
ምንም እንኳ የጉራጌ ዞን ም/ቤት በመንግስት የቀረበለትን በነባሩ ደቡብ ክልል እንዲቆይ የሚጠይቀውን ሀሳብ ውድቅ ቢያደርግም፤ በፌደሬሽን ም/ቤት ባለበት እንዲቆይ ተወስኗል፡፡
የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የክልል ጥያቄዎች በብዛት የተነሱበት ክልል ሲሆን፤ ለአራት ተከፋፍሎ እንዲደራጅ በብልጽግና ፓርቲ አቋም ተይዟል፡፡
የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ለአል ዐይን የክልል ጥያቄ ከመልካም አስተዳደርና ከፍትኃዊ ተጠቃሚነት ጋር ተያይዞ ቢነሳም ፓርቲው ምላሽ በሚሰጠው ልክ ምላሽ ሰጥቷል ሲሉ የጉራጌ የክልል እጣ ፈንታ የተለየ እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ከዞኑ ኅብረተሰብ ጋር ለመወያየት ዛሬ ጠዋት ጉራጌ ዞን መግባቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል።