በኢትዮጵያ በአደጋዎች ምክንያት "ማህበራዊ ጥበቃ" ፈላጊዎች እየጨመሩ ነው ተባለ
ኢሰመኮ በቅርቡ የጎና ተዳዳሪዎች ህግን ባልተከተለ መንገድ መነሳታቸው ተገቢ አይደለም የሚል ሪፖርት አውጥቶ ነበር

ደሀና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአገልግሎታቸው የማያካትቱ ተቋማትን ተጠያቂ ሊሆኑ ነው
በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ማህበራዊ ጥበቃ የሚሹ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል
"ተጋላጭ" የሆኑና ማህበራዊ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከፍተኛ መሆናቸውን የጠቀሰው ሚንስቴሩ፤ በየጊዜው የሚገሰቱ አደጋዎችና ሌሎች ችግሮች ከለላውን ውስን አድርጎታል ብሏል።
ሀገሪቱ በ2007 ዓ.ም. የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ብትቀርጽም ከተቋማት ጋር አለመሳለጥ ጥበቃ ለሚሹ ዜጎች ተደራሽነትን ፈታኝ ማድረጉን ሚንስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ለዚህም ግንዛቤ ለመፍጠርና ለተቋማት ትስስር ሚና አለው የተባለ ጉባኤ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚካሄድ ሚንስትሯ ገልጸዋል።
ከስምንት ዓመት በፊት የወጣው የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ እንዲከለስ ነባራዊ ሁኔታው አስገድዷልም ተብሏል።
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የህዝብ ቁጥር ብዛትና አደጋዎች መጨመር ለማሻሻል ገፊ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የሴፍቲ ኔትና የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳት መርሀ-ግብሮች በአብነት የሚጠቀሱ ውጤታማ የሚባሉ የማህበራዊ ጥበቃ ስራዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የጸጥታ ኃይሎች የጎዳና ተዳዳሪዎችን ህግ ባልተከተለ መንገድ ማፈሳቸውን አስታውቋል።
ሚንስትሯ ካለፍላጎት ማንም (ሰው) መነሳት የለበትም ብለዋል።
ችግሮች ካለመናበብ እንደሚከሰቱ ጠቁመው፤ በመርሀ-ግብሩ ከ22 ሽህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች የተነሱበት ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
ማህበራዊ ጥበቃ የማይመለከተው ተቋም የለም ያሉት ሚንስትሯ፤ ደሀና ተጋላጮችን የማያካትቱ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ ስራ ስለመጀመሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጽያ የማህበራዊ ጥበቃ ደረጃ እንደ ምጣኔ-ሀብቷና ነባራዊ ሁኔታዋ የሚታይ መሆኑን የጠቀሱት ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ ልገሳ ላይ የተመሰረተ አካሄድ አንጠቀምም ብለዋል።
ተጋላጭ ሰዎች በእግራቸው እስኪቆሙ ድረስ መደገፍ በመንግስታቸው የተመረጠ አካሄድ መሆኑን አንስተዋል።
ሚንስትሯ ከዓለም አቀፍ ልማት አጋሮች ድጋፍ ለመላቀቅ ያለሙ ውጥኖች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።