ኢትዮጵያ በሊማ ከ20 ዓመት የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ከዓለም 2ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀች
6 ወርቅን ጨምሮ በ10 ሜዳሊያዎችን ያገኘችው ኢትዮጵያ በሜዳሊያ ብዛት አሜሪካን በመከተል ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች
በፓሪስ ፓራሊምፒክም ኢትዮጵያ የወርቅ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ አግኝታለች
በፔሩ ሊማ በተካሄደው የአለም ከ20 አመት በታች የአትሌቲክ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀቀች።
በፔሩ፣ ሊማ ከነሃሴ 21 ጀምሮ ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ትናት ሌሊት ፍጻሜውን አግኝቷል።
ኢትዮጵያን በመወከል የተሳተፈው ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በ6 ወርቅ፣ 2 ብር እና 2 ነሐስ በአጠቃላይ 10 ሜዳሊያዎችን ማሸነፍ ችሏል።
በዚህ ኢትዮጵያ ከዓለም አሜሪካን በመከተል 2ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ያጠናቀቀች ሲሆን፤ ውድድሩን 1ኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀች አሜሪካ በ8 ወርቅ፣ 4 ብር እና 4 ነሃስ በድምሩ 16 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።
ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ አትሌቶች
በአትሌት መዲና ኢሳ በ5000 ሜትር፣
በአትሌት ሲምቦ አለማየሁ በ3000 ሜትር መሰናክል
በአትሌት ጀነራል ብርሃኑ በ800 ሜትር፣
በአትሌት አለሺኝ ባወቀ በ3000 ሜትር ሴቶች
በአትሌት ሳሮን በርሀ በ1500 ሜትር እና
በአትሌት አብዲሳ ፈይሳ በ1500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝተዋል።
በተጨማሪም አትሌት መቅደስ ዓለምእሸት እና አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በተመሳሳይ ርቀት በ5000 ሜትር የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ አስገኝተዋል ።
አትሌት ማርታ አለማየሁ በ3000 ሜትር ሴቶችና አትሌት ኃይሉ አያሌው በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግበዋል ።
በዚህ ሻምፒዮና በ800 ሜትር፣ በ1500 ሜትር፣ በ3000 ሜትር፣ በ5000 ሜትር፣ በ3000 ሜትር መሠናክል በሁለቱም ፆታ እንዲሁም በ10000 ሜትር ሴቶች እርምጃ 11 ሴት፣ 8 ወንድ በአጠቃላይ 19 አትሌቶች ኢትዮጵያን ወክለው መሳተፋውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያለክታል።
በፔሩ ሊማ በተካሄደው የአለም ከ20 አመት በታች የአትሌቲክ ሻምፒዮና 134 ሀገራትን በተሳተፋበት ሲሆን፤ 34 ሃገራት በሜዳልያ ሰንጠረዥ መግባ ችለዋል።
በሌላ ዜና ኢትዮጵያ በፓሪስ ፓራሊምፒክ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አሸንፋለች።
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ለኢትዮጵያ በ2024ቱ የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ አስገኝታለች።
ለ17ኛ ጊዜ በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ በሚገኘው የፓራሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ በ 1,500 ሜትር ጭላንጭል ውድድር በአትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ አማካኝነት ማግኘት ችላለች ።
አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ በፓራሊምፒክ ውድድር ታሪክ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳልያ ያመጣች ሲሆን ከሶስት አመታት በፊት በቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር በተመሳሳይ ርቀት ለ ሀገራችን በታሪክ የመጀመሪያ የ ፓራሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘት ችላለች ።