በሶማሊያ የመንገደኞች አውሮፕላን ተገለበጠ
አውሮፕላኑ የመገልበጥ አደጋ ያጋጠመው 33 መንገደኞችን ከባይደዋ ወደ ሞቃዲሾ ሲያጓጉዝ ነው
አውሮፕላኑ በሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ እያረፈ ባለበት ነው የመገልበጥ አደጋ ያጋጠመው
በሶማሊያ የመንገደኞች አውሮፕላን በማረፍ ላይ እያለ ባጋጠመው አደጋ ተገለበጠ፡፡
በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን የመገልበጥ አደጋ ማስተናገዱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አደጋው ያጠመው የሀገር ውስጥ መንገደኞችን በማጓጓዝ ላይ የነበረ አውሮፕላን ሲሆን 33 መንገደኞችን ከባይደዋ ወደ ሀገሪቱ መዲና ሞቃዲሾ በማጓጓዝ ላይ ነበር፡፡
ይህ የመንገደኞች አውሮፕላን በሞቃዲሾ አውሮፕላን ማረፊያ በማረፍ ላይ ሳለ ባጋጠመው ግጭት ምክንያት የተገለበጠ ሲሆን በሁሉም ተሳፋሪዎች ላይ ያጋጠመ የጎላ ጉዳት እንደሌለ የሶማሊያ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡
አውሮፕላኑ ጁባ አየር መንገድ እንደሚባል የተገለጸ ሲሆን ስለ አውሮፕላኑ አደጋ መንስኤ እስካሁን ምንም የወጣ መረጃ የለም፡፡
በሶማሊያ የአውሮፕላን አደጋ የተለመደ ሲሆን፤ ወደ ሞቃዲሾ የሚበሩ የተለያዩ ሀገራት አውሮፕላኖች ተደጋጋሚ የመከስከስ አደጋዎች ያጋጥማሉ፡፡
የአልሻባብ የሽብር ጥቃት ባዳከማት ሶማሊያ የአውሮፕላን በረራ ተመራጭ የትራንስፖርት መንገድ ቢሆንም ተደጋጋሚ የአውሮፕላን አደጋዎች መከሰት ሌላኛው የተጓዦች ስጋት ሆኗል።
ከዚህ በፊት የኬንያ የግል የመንገደኞች እና የጭነት አውሮፕላኖች በተደጋጋሚ አደጋዎችን በሶማሊያ ያስተናገዱ ሲሆን ከጥቂት አየር መንገዶች በስተቀር በርካታ አየር መንገዶች ወደ ሶማሊያ የሚያደርጉትን በረራዎች አቋርጠዋል።