የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ የነፍስ አድን ዘመቻው በተረጋጋ መንፈስ እንዲካሄድ ጠቀዋል
ንብረትነቱ የፕሪሲዥን ኤር የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን በታንዛኒያ ቪክቶሪያ ሀይቅ ላይ መከስከሱ ተገለጸ፡፡
አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በቡኮባ አየር አውሮፕላን ማረፊያ ለማረፍ ሲሞክር ባጋጠመው መጥፎ የአየር ጠባይ( በቪክቶሪያ ሀይቅ በጣለው ከባድ ዝናብ) ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
የመንግስት ንብረት የሆነው የታንዛኒያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ቲቢሲ) እንደዘገበው ከሆነ በአውሮፓኑ ውስጥ 43 ሰዎች የነበሩ ሲሆን እስካሁን የ15 ሰዎች ህይወት ማዳን ተችሏል፡፡ ነገር ግን የሞት አደጋ ስለመኖሩ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡
የካጄራ ግዛት ፖሊስ አዛዥ ዊልያም ምዋምፓጋሌ “በርካታ ሰዎችን ማዳን ችለናል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
“አውሮፕላኑ 328 ጫማ ሲደርስ ችግሮች እና መጥፎ የአየር ሁኔታ አጋጥመውታል። ዝናብ እየዘነበ ነበር እና አውሮፕላኑ ወደ ውሃው ውስጥ ገባ፤ አሁን ሁሉም ነገር በቁጥጥር ስር ነው”ም ብለዋል አዛዡ፡፡
የዜና አውታሮች አውሮፕላኑ ሀይቅ ውስጥ ሰምጦ የሚያሳዩ ፎቶዎችን በማሳየት ላይ ናቸው፡፡
የነፍስ አድን ጀልባዎች ተሰማርተው የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በአውሮፕላኑ ውስጥ የተሳፈሩትን ሌሎች መንገደኞች የማዳን ስራቸው በማከናወን ላይ መሆናቸውንም ዘግበዋል፡፡
የቡኮባ አየር ማረፊያ በአፍሪካ ትልቁ ሀይቅ በቪክቶሪያ ሀይቅ ዳርቻ ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን በአደጋው የተሰማቸው ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡
"የፕሪሲዥን ኤር አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋን የተመለከተ አሳዛኝ ዜና ደርሶኛል" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንቷ፤ የነፍስ አድን ዘመቻው በተረጋጋ መንፈስ እንዲካሄድ ጠቀዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በበኩላቸው በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ማዘናቸው ገልጸው ለታንዛንያውያን መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
“በቪክቶሪያ ሃይቅ ላይ በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍረው የነበሩትን መንገደኞች ቤተሰቦች መጽናናት እንመኛለን”ም ብለዋል ሊቀ መንበሩ፡፡