ኡጋንዳ በታሪኳ በሴቶች የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች
አትሌት ፔሩዝ ቼሙታይ በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ሩጫ ለሀገሯ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች
ኡጋንዳ ባሳለፍነው ሳምንት በወንዶች 10000 ሜትር የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል
ኡጋንዳዊቷ አትሌት ፔሩዝ ቼሙታይ በቶክዮ ኦሎምፒክ የሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ሩጫ ለሀገሯ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
ፔሩዝ ቼሙታይ የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት በኡጋንዳ የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት በመሆንም ለሀገሯ አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችላለች።
የ22 ዓመቷ ፔሩዝ የሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ሩጫ ውድድሩን 9:01.45 ሰዓት በመግባት በአንደኝነት ማጠናቀቅ ችላለች።
ውድድሩን አሜሪካዊቷ ካርተኒ ፍሬሪችስ 9:04.79 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅቀ ኬንያዊቷ ሐይቪን ኪዬንግ 9:05.39 ሰዓት በመግባት 3ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በዚህ ውድድር የተሳተፉት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መቅደስ አበበ 4ኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ፤ አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ 8ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።
የ22 ዓመቷ ኡጋንዳዊቷ አትሌት ፔሩዝ ቼሙታይ በዛሬው ውድድር ርቀቱን የጨረሰችበት ሰዓት የሀገሯ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦላታል።
አትሌት ፔሩዝ ቼሙታይ በርቀቱ ለሀገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቷን ተከትሎም ኡጋንዳውያን ደስታቸውን በተለያየ መልኩ እየገለጹ ነው።
ኡጋዳ ባሳለፍነው ሳምንት በወንዶች 10000 ሜትር በአትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ የብር ሜዳሊያ፤ በአትሌቱ ጃኮፕ ኪፕሊሞ የነሃስ ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል።
ኡጋንዳ በእስካሁን የኦሎምፒክ ታሪኳ (የቶኪዮ ኦሎምፒክን ጨምሮ) 3 የወርቅ፣ 4 የብር እና 3 የነሃስ በድምሩ 10 ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች።
በኦሎምፒክ መድረክ ለመጨረሻ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ ማንሳት የቻለችውም በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ እንደነበረም መረጃዎች ያመለክታሉ።