አትሌቶች በከፍተኛ ዝላይ እኩል ነጥብ በማምጣታቸው ነው ሜዳሊያ የተጋሩት
በቶኪዮ ኦሎምፒክ የጣሊያን እና የኳታር የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪዎች በአትሌቲክስ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ መጋራታቸውን የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል።
ጣሊያናዊው ጂያን ማርኮ ታምቤሪ እና የኳታሩ ሙታዝ ባርሺም ባደረጉት የከፍታ ዝላይ ውድድር አሸናፊውን መለየት ስላልተቻለ የወርቅ ሜዳሊያ ለመጋራት መስማማታቸው ተገልጿል።
ውጤታቸውን በግልጽ መለየት ስላልተቻለ አትሌቶቹን ምን መደረግ እንዳለበት ተጠይቀው እንደነበር ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ገልጿል።
የኳታሩ አትሌት ሙታዝ ባርሺም እና ሁለት ውርቅ ሜዳሊያዎች ለሁለቱ አትሌቶች ቢሰጡ የሚል ሃሳብ በማቅረቡ የአትሌቲክስ ኃላፊዎችም ይህንን ተቀብለውታል ነው የተባለው።
ሙታዝ ባርሺም ያቀረበውን ሃሳብ ጣሊያናዊው ጂያን ማርኮ ታምቤሪም እንደተቀበለው ተገልጿል፤ በዚህም መሰረት ውጤታቸው ተመሳሳይ ለሆኑት ሁለቱም አትሌቶች የወርቅ ሜዳሊያ ተሰጥቷቸዋል።
ሁለቱም አትሌቶች ይህንን ታሪክ መጋራት በመቻላቸው መደሰታቸውን አስታውቀዋል።
አትሌቶቹ ለደቂቃዎች በመተቃቀፍ የኦሊምፒክ ምንነትና ትርጉምን አሳይተዋል በሚልም እየተወደሱ መሆናቸው ተገልጿል።
ይህ የወርቅ ሜዳሊያን የመጋራት ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ መሆኑ ቀጥሏል፡፡ ለትውልድም ወንድማማችነትን እንደሚያስተምርም ነው እየተገለጸ ያለው።