ፊሊፖ ግራንዲ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሆነው በድጋሚ ተመረጡ
ዩኤንኤችሲአር በግዳጅ የተፈናሉና ሀገር አልባ የሆኑ ስደተኞች የሚረዳ ድርጅት ነው
ፊሊፖ ግራንዲ ከሃምሌ 1ቀን 2023 ጀምሮ ለሁለት አመት ተኩል የዩኤንኤችሲአር ኮሚሽነር ሆነው የሚያገለግሉ ይሆናል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ጣሊያናዊው ዲፕሎማት ፊሊፖ ግራንዲን የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) አድርጎ መረጠ፡፡
ፊሊፖ ግራንዲ ከሃምሌ 1ቀን 2023 እስኪ ታህሳስ 31 ቀን 2015 የተመድ ኤጀንሲው ከፍተኛ ኮሚሽነር ሆነው በድጋሚ እንደሚያገልግሉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ፊሊፖ ግራንዲ እንደፈረንጆቹ ጥር 1ቀን፤2016 ጀምሮ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ፊሊፖ ግራንዲ በፈረንጀቹ 2016 ወደ ኃላፊነት ሲመጡ የአሁኑ የተመድ ዋና ጸሃፊ አነቶኒዮ ጉቴሬዝ በመተካት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በተጨማሪም ፊሊፖ ግራንዲ ከጥር 2010 እስከ መጋቢት 2014 በነበሩ ጊዜያት፤ የተመድ የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲን ሲመሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ማህበረሰቦችን እና ሀገር አልባ ሰዎችን ለመርዳት እንዲሁም በፈቃደኝነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አልያም በተሰደዱበት አካባቢው እንዲቀላቀሉ ወይም ወደ ሶስተኛ ሀገር እንዲሰፍሩ የሚያስችል አስፈላጊውን እርዳታ ለማድረግ የተቋቋመ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ነው።
ድርጅቱ፤ ከ27 ሀገራት የመጡ ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ ስደተኞችን ከምታስተናግደው ኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም የሚታወቅ ነው፡፡