አረብ ኢምሬትስ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች ድጋፍ የሚሆን 5 ሚሊዮን ዶላር ሰጠች
ድጋፉ ከ 6 እስከ 23 ወር እድሜ ያላቸው ወደ 38 ሺ የሚጠጉ ህጻናትን ተጠቃሚ የሚያደረግ ነው ተብሏል
በኢትዮጵያ ለስደተኞች የሚሰጠውን የምግብ እርዳታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ 50 በመቶ መቀነሱ መረጃዎች ይጠቁማሉ
አረብ ኢምሬትስ በኢትዮጵያ የሚገኙትን ስደተኞች እየረዳች መሆኗን የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ምክትል ተወካይ ማርጋሬት ማርጋሬት አቲኖ አሁን ላይ በተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ /ዩኤንኤችኤችአር/ እና አጋሮቹ አማካኝነት ከ740ሺ በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች አየተሰጠ ካለው የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ድጋፍ ውስጥ 5ሚሊየን ዶላር የሸፈነው የአረብ ኢምሬትስ መንግስት ነው ብለዋል፡፡
"የግብአት ውስንነት ማጋጠሙን ተከተሎ ለስደተኞች የሚሰጠውን የምግብ ራሽን እንዲቀንስ በሚያስገድድበት በዚህ ወቅት አረብ ኢምሬትስ ህዝብ እና መንግስት ላደረጉት ድጋፍ ዩኤንኤችሲአር ምስጋናውን ያቀርባል”ም ነው ያሉት ምክትል ተወካይዋ፡፡
ማርጋሬት "ይህ እርዳታ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ ተያያዥ የጤና ችግሮችን እና ሞትን ለመቀነስ አስተዋጽዖ ያደርጋል" ሲሉ መናገራቸውም የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ አትቷል፡፡
በፋሚን ረሊፍ ፈንድ (ኤፍአርኤፍ) በኩል የቀረበው የገንዘብ ድጋፉ ለሁሉም ስደተኞች የሚደረግ ወርሃዊ የምግብ ስርጭት ለማስቀጠል እና ዩኤንኤችኤችአር የጀመረውን የልዩ የአመጋገብ መርሃ ግብር እንዲያካሂድ የሚያስችል ነው ተብሎለታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ድጋፉ ከ 6 እስከ 23 ወር እድሜ ያላቸው ወደ 38 ሺ የሚጠጉ ህጻናት እና ከ 27 ሺህ በላይ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደረግ ነው።
ኢትዮጵያ አስከፊ ድርቅ ከተጋረጠባቸው የቀጣናው ሀገራት አንዷ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ይህም በዩክሬን ያጋጠመው ጦርነትን ተከትሎ ካጋጠመው የምግብ እና የሸቀጦች ዋጋ መናር ጋር ተዳምሮ በሀገሪቱ ያለው የምግብ እጥረት እጅጉን እንዳባበሰው ይገለጻል፡፡
ይህም በኢትዮጵያ ለስደተኞች የሚሰጠውን የምግብ እርዳታና አቅርቦት በገንዘብ እጥረት ምክንያት ወደ 50 በመቶ ብቻ እንዲቀንስ ማድረጉ የተመድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡