በውስጡ 85 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የፊሊፒንስ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከሰከሰ
“C130” አውሮፕላኑ በሱሉ ግዛቷ ጆሎ ለማረፍ ሲል ከመንድርደሪያው ወጥቶ ነው የተከሰከሰው
በአውሮፕላን አደጋው እስካሁን የ17 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች አስታውቀዋል
በውስጡ 85 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የነበረ የፊሊፒንስ ወታደራዊ አውሮፕላን መከስከሱን የሀገሪቱ ጦር አስታወቋል።
አውሮፕላኑ በፊሊፒንስ ደቡባዊ ክፍል ላይ መከስከሱንም ነው ጦሩ በዛሬው እለት ያስታወቀው።
የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጄነራል ሰርሊቶ ሶበሃና እንዳስታወቁት፤ “C130” የሚል መጠሪያ ያለው አውሮፕላኑ በሱሉ ግዛት ጆሎ በተባለ ስፍራ ለማረፍ በሚሞክርበት ወቅት ከመንድርደሪያው ወጥቶ ነው የተከሰከሰው።
እስካሁንም የ17 ሰዎች አስከሬን አውሮፕላኑ ከተከሰከሰበት ስፍራ መገኘቱንም ነው ጦሩ ያስታወቀው።
ከአደጋው የተረፉ ከ40 በላይ ሰዎችም ለህክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ነው የጦሩ አዛዥ ጄነራል ሰርሊቶ ሶበሃና የተናሩት።
በአሁኑ ወቅትም አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ስፍራ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጭስ እና እሳት እንደሚታይም ነው በስፍራው ያሉ አይን እማኞች የሚናገሩት።
“C130” የሚል መጠሪያ ያለው አውሮፕላን የፊሊፒንስ አየር ሀይል በቅርቡ ካገኛቸው ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖች ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወቃል።
አውሮፕላኑ ለሀገሪቱ አየር ሀይል በርካታ ግልጋሎቶችን እንደሚሰጥ የተነገረ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ወታደሮችን እና ግብዓት ማጓጓዝ አንዱ ተግበሩ ነው።
በሀገሪቱ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅትም አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፎችን ለተጎጂዎች የማድረስ አገልግሎትን ይሰጥ እንደነበረም ነው የተገለጸው።