በኔፓል በደረሰ የአውሮፕላን አደጋ አብራሪው በህይወት ሲተርፍ 18 ሰዎች ሞቱ
ደካማ የአየር ደህንነት ቁጥጥር አላት በምትባለው ኔፓል ባለፈው አመት በአውሮፕላን አደጋ 72 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል
የተከሰከሰው አውሮፕላን ለረጂም ጊዜ ከአገልግሎት ውጭ ሆነ የቆየ የመንገደኞች አውሮፕላን ነው
ከኔፓል ዋና ከተማ ካታማንዱ በመነሳት ላይ እያለ አደጋ ባጋጠመው አውሮፕላን የ18 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተሰምቷል፡፡
የሳውርያ አየር መንገድ ንበረት እንደሆነ የተነገረለት አውሮፕላን ለሙከራ በረራ 17 ቴክኒሻኖችን እና ሁለት የበረራ አስተናጋጆችን ይዞ መብረር እንደጀመረ በአውሮፕላን ማረፍያው አቅራቢያ መከስከሱ ነው የተነገረው፡፡
አውሮፕላኑ በቅርቡ ስራ ወደ ጀመረው ፖክሃራ አየር ማረፊያ በማቅናት ላይ እያለ አደጋው የገጠመው ሲሆን በአደጋው አውሮፕላን አብራሪው ብቻ በህይወት ሲተርፍ 18 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡
ከአውሮፕላን ማኮብኮብያ በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በተከሰከሰው አውሮፕላን ሞተር ላይ የተፈጠረው እሳት ለአደጋው መባባስ ምክንያት እንደሆነ የሀገሪቱ ሲቪል አቭየሽን ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አደጋ የደረሰበት አየር መንገድ በጊዜያዊነት ሙሉ ለሙሉ ስራ ማቆሙ ሲገለጽ ከአደጋው የተረፈው አውሮፕላን አብራሪ በሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል፡፡
50 ሰዎችን የመጫን አቅም ያለው CRJ200 የተባለው አውሮፕላን ለረጅም ጊዜ ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ የቆየ አውሮፕላን እንደነበር ታውቋል፡፡
በ2014 የተመሰረተው ሳውርያ አየር መንገድ በአምስት የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች ላይ የሚሰራ ሲሆን እነዚህን አነስተኛ አውሮፕላኖች ለሀገር ውስጥ በረራ ለመጠቀም የተለያዩ ጥገናዎችን በማድረግ የፍተሻ በረራዎችን በማድረግ ላይ እንደነበር ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
በደካማ የአየር ደህንነት ቁጥጥር የምትታማው ኔፓል ከፈረንጆቹ 2000 ጀምሮ በተለያዩ የአውሮፕላን እና የሄሊኮፕተር አደጋዎች 350 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተውባታል፡፡
ሀገሪቱ አስከፊ የሚባለው የአውሮፕላን አደጋ የተከሰተባት በ1992 ሲሆን የፓኪስታን አየር መንገድ ንበረት የሆነው ኤርባስ አውሮፕላን በተራራማ አካባቢዎች ተከስክሶ በአደጋው 167 ሰዎች ሞተዋል ፤ በተጨማሪም በባለፈው አመት ጥር ወር ላይ በተከሰተ አደጋ 72 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡