የጀራርድ ፒኬ የ14 አመታት የባርሴሎና ቆይታ በኑ ካምፕ ሽኝት ተደመደመ
ፒኬ በፈረንጆቹ 2008 ነበር ከማንቸስተር ዩናይትድ የስፔኑን ክለብ የተቀላቀለው
ፒኬ በ10 አመት ከምትበልጠው የላቲን ሙዚቃ ኮከቧ ሻኪራ ጋር የመሰረተው ትዳር መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል
የጀራርድ ፒኬ የ14 አመታት የባርሴሎና ቆይታ በኑ ካምፕ ሽኝት ተደመምድሟል።
ባርሴሎና አልሜሪያን 2 ለ 0 ባሸነፈበት ጨዋት 84ኛው ደቂቃ ላይ የተቀየረው ፒኬ የቡድን አጋሮቹን እና አሰልጣኙን ዣቪ ሄርናንዴዝ በእምባ ታጅቦ ተሰናብቷል።
በኑ ካምፕ የታደሙ የባርሴሎና ደጋፊዎችም አንፀባራቂ ጊዜን ላሳለፈው ተጫዋች የሚገባውን ክብር ሰጥተውታል።የ35 አመቱ ስፔናዊ "የተወለድኩት እዚህ ነው የምሞተውም በዚህ ነው" ሲል ለባርሴሎና ያለውን ፍቅር ገልጿል።
ለባርሴሎና 53 ግቦችን ያስቆጠረው ፒኬ በትናንቱ የአልሜሪያ ግጥሚያ ጎል አግብቶ ስንብቱ የደመቀ እንዲሆን ቢታሰብም አልተሳካም።
የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዬላን ጨምሮ በርካታ አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች ስለ ፒኬ ድንቅ ብቃትና ስብእና በትዊተር ገፃቸው በማስፈር ላይ ናቸው።
ለአራት አመት ያሰለጠኑት ጋርዲዬላ "ፒኬ ህልሙን ኖሯል፤ ለትልቅ ክለብ የሚመጥን ብቃትና ስብእና ያለው ተጫዋች ነው፤ እሱን በማሰልጠኔ ክብር ይሰማኛል" ብለዋል።
ፒኬ ከስምምነቱ 18 ወራት እየቀረው መልቀቁ የካታላኑን ክለብ የፋይናንስ ቀውስ ረገብ እንደሚያደርገው ይታመናል።
ቁመተ ለግላጋው ተጫዋች ከሊዬኔል ሜሲ፣ ዣቪ ሄርናንዴዝ፣ ሰርጂዬ ቡስኬትና አንድሪየስ ኢኔሽታ በመቀጠል በባርሴሎና 5ኛው በርካታ ጨዋታዎችን ያደረገ ተጫዋች ነው።
በክለቡ 616 ጊዜ ተሰልፎ 30 ዋንጫዎችን ያነሳው ፒኬ፥ በፈረንጆቹ 2008 ነበር ከማንቸስተር ዩናይትድ የስፔኑን ክለብ የተቀላቀለው።
በ2007-08 የውድድር አመት የቻምፒዮንስ ሊግ፣ ፕሪሚየር ሊግ እና ኮሚዩኒቲ ሺልድ ዋንጫ ያነሳው የቀያይ ሰይጣኖቹ ስብስብ አባል የነበረው ፒኬ ለሀገሩ ስፔንም ከ100 በላይ ጨዋታዎች ተሰልፏል።
ፒኬ በስፔን ሁለተኛ ሊግ የሚጫወተው ኤፍ ሲ አንዶራ ክለብ ባለቤት ነው።ጀራርድ ፒኬ ከእግር ኳስ ታሪኩ ባሻገር ከኮሎምቢያዊቷ አቀንቃኝ ሻኪራ ጋር በ2010 የመሰረተው ትዳር መነጋገሪያ ነበር።