የሩሲያ ጦር ኮማንደሮች በኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ላይ መምከራቸው ተገለጸ
አሜሪካ በበኩሏ እስካሁን ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ለመጠቀም ስለማሰቧ መረጃ የለም ብላለች
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ፑቲን የሞስኮ ደህንነት አደጋ ውስጥ ከገባ ብቻ ኑክሌር እንጠቀማለን ማለታቸው ይታወሳል
የሩሲያ ጦር ኮማንደሮች በኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ላይ መምከራቸው ተገለጸ፡፡
ዩክሬን ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ የሩሲያ ጦር ለቀናት ለሚቆይ ልዩ ዘመቻ ለማድረግ በሚል ወደ ዩክሬን ከገባ ስምንት ወራት አልፎታል፡፡
ይህ ጦርነት በየጊዜው አዳዲስ ክስተቶችን በማስተናገድ ላይ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል የሚለው ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል፡፡
የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ባወጣው መረጃ መሰረት የሩሲያ ጦር ኮማንደሮች የኑክሌር ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ስለማዋል መምከራቸውን አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን አልተሳተፉበትም በተባለው በዚህ ውይይት ላይ የሞስኮ የጦር አዘዦች በዩክሬን ምድር የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ስለመጠቀም እንደተወያዩ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ ጦር መሪዎች ከዩክሬን ጋር እያደረጉት ባለው ጦርነት ዙሪያ እንዴት እና መቼ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን መጠቀም እንዳለባቸው ተወያይተዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ነጩ ቤተመንግስት በበኩሉ ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎችን በዩክሬን ልትጠቀም ትችላለች በሚል ስጋት እንደገባው ከዚህ በፊት ገልጾ ነበር፡፡
ይሁንና አሁን ላይ ባወጣው መረጃ ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ በዩክሬን ለመጠቀም ስለማቀዷ ምንም አይነት መረጃ እንዳላገኘ አስታውቋል፡፡
ሩሲያ አሁን ላይ የኑክሌር ጦር መሳሪያዋ ቀድሞ ከተቀመጠበት አለማንቀሳቀሷን ያስታወቀችው አሜሪካ በዩክሬንም ይሄንን አውዳሚ የጦር መሳሪያ እንደምትጠቀም ፍንጭ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ በፊት እንዳሉት ሞስኮ የኑክሌር የጦር መሳሪያዋን የምትጠቀመው ብሄራዊ የደህንነት አደጋ ከተደቀነባት ብቻ እንደሚሆን መናገራቸው ይታወሳል፡፡