ትናንት በተካሔዱ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቼልሲ ሲሸነፍ ማን. ዩናይትድ ነጥብ ጥሏል
በፕሪሚየር ሊጉ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ከማን ምን ይጠበቃል?
ቼልሲ ከሜዳው ዉጭ በአንፊልድ ከሊቨርፑል ጋር ባደረገው ጨዋታ 5 ለ 3 በመሸነፍ የመጨረሻ 4 ዉስጥ ለመጨረስ ጫና ዉስጥ ገብቷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተዳከመ የመጣው ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ በሜዳው ዌስት ሃም ዩናይትድን አስተናግዶ 1 ለ 1 ተለያይቷል፡፡ ይሁንና ቼልሲ በመሸነፉ እኩል 63 ነጥብ ቢኖራቸውም በጎል ብልጫ ማንችስተር ዩናይትድ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ሊቨርፑል ከ30 ዓመታት ትዕግስት በኋላ ዋንጫውን ሲያነሳ ማንችስተር ሲቲ 2ኛ ሆኖ ማጠናቀቁን አረጋግጧል፡፡
ማን. ሲቲ ለሁለት ዓመታት በሻምፒዮንስ ሊግ እንዳይሳተፍ የተጣለበት እገዳ እንዲነሳለት ያቀረበው አቤቱታ በቅርቡ ተቀባይነት አግኝቶ ክለቡ ተሳታፊነቱን ማረጋገጡ ፣ ከ3ዓ-5ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙ የሊጉ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊግ የመሳተፍ እድልን ማን ሊያገኝ ይችላል የሚለውን ጥያቄ አጓጊ አድርጎታል፡፡
በቀጣዩ እሁድ በሚደረገው የውድድር ዓመቱ የመጨረሻው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ዩናይትድ ከሜዳው ዉጭ ከሌይስስተር እንዲሁም ቼልሲ በሜዳው ከዎልቨርሀምፕተን ጋር በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች 3ኛ እና 4ኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦችን ይለያሉ፡፡
ማንችስትር 3ኛ አሊያም 4ኛ ሆኖ ለማጠናቀቅ 1 ነጥብ በቂው ነው፡፡ ቼልሲ ሽንፈትን ካስተናገደ ማንችስተር 3ኛ ሆኖ ለመጨረስ አቻ መውጣት ይበቃዋል፡፡ ሌይስስተርን የሚያሸንፍ ከሆነ ደግሞ የማንንም ዉጤት ሳይጠብቅ 3ኛ ደረጃን ይዞ በመጨረስ በቀጥታ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ይሆናል፡፡
ከማንችስተር እና ከቼልሲ በ1 ነጥብ አንሶ በ62 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሌይስስተር ሲቲ የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ለማግኘት ማሸነፍ አሊያም ከማንችስተር ጋር አቻ ወጥቶ ቼልሲ ሊሸነፍለት ይገባል፡፡
ቼልሲ በበኩሉ ከዎልቭስ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ አሸንፎ ማንችስተር ቢሸነፍ አሊያም አቻ ቢወጣ 3ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ይችላል፡፡ ቼልሲ ከተጋጣሚው አቻ ከተለያየ ደግሞ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ለመጨረስ ከሌይስስተር እና ማንችስተር ጨዋታ አቻ ነጥብ አሊያም መሸናነፋቸውን ይፈልጋል፡፡ ቼልሲ የሚሸነፍ ከሆነ ደግሞ ለ4ኛው ደረጃ ማንችስተር ሌይስስተርን እንዲያሸንፍለት ይፈልጋል፡፡
በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ ሌሎች አማራጮች
ማንችስተር ዩናይትድ በመጨረሻው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታው የሻምፒዮንስ ሊግ ቦታን ማሳካት ቢሳነው ፣ ቦታውን ለማግኘት የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ሊያሸንፍ ይገባዋል፡፡ ቼልሲ ደግሞ በውድድር ዉስጥ የሚገኝበትን የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ማሸነፍ ከቻለ ለቀጣዩ ሻምፒዮንስ ሊግ በቀጥታ መሳተፍ ይችላል፡፡ ሌይስስተር ሲቲ ግን ሌላ አማራጭ የለውም፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት ክለቦች ዉጭ ዎልቭስ የዩሮፓ ሊግን ማሸነፍ ከቻለ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ቦታን ማግኘት ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ ዎልቭስ ዩሮፓ ሊግን ካሸነፈ እና ቼልሲ በፕሪሚየር ሊጉ ከቀዳሚ 4 (Top 4) ዉጭ ሆኖ ሻምፒዮንስ ሊግን ካሸነፈ ከማንችስተር ዩናይትድ እና ከሌይስስተር ሲቲ 4ኛ ሆኖ የሚጨርሰው ክለብ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ቦታን ያጣል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከእንግሊዝ ከ 5 ክለብ በላይ በሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፍ ስለማይችል ነው፡፡ የዚህ ሁሉ እንቆቅልሽ እንዲፈታ ታዲያ ቼልሲ 4ኛ ሆኖ ካልጨረሰ የዘንድሮውን የሻምፒዮንስ እና የዩሮፓ ሊግ ዋንጫ ጉዞ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡
ያም ሆኖ እሁድ እለት በሚደረገው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ 3ኛ ሆኖ የሚጨርሰው ክለብ በቀጥታ ለቀጣዩ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊነት ትኬቱን ይቆርጣል፡፡ 4ኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ክለብ ደግሞ ተሳታፊነቱን ለማረጋገጥ ቢያንስ በሻምፒዮንስ ሊግ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ቼልሲ ከባየር ሙኒክ ጋር የሚያደርገውን የመልስ ጨዋታ ይጠብቃል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ከሜዳው ዉጭ በሙኒክ 3 ለ ባዶ የተሸነፈው ቼልሲ ዉጤቱን ቀልብሶ ማለፍ ካልቻለ በፕሪሚየር ሊጉ ከዩናይትድ እና ሌይስስተር 4ኛ ሆኖ ሚያጠናቅቀው ክለብ (ከሌላ ሀገር ክለብ ጋር በሚያደርገው የደርሶ መልስ የጨዋታ ዉጤት) ሻምፒዮንስ ሊግ የሚሳተፍበትን እድል ያገኛል፡፡