በካናዳ የመንገደኞች አውሮፕላን ተገልብጦ 18 ሰዎች ቆሰሉ
ከአሜሪካ ሚኒያፖሊስ 80 ሰዎችን አሳፍሮ ወደ ካናዳ ሲጓዝ የነበረው የዴልታ አየርመንገድ አውሮፕላን በቶሮንቶ ሲያርፍ ነው አደጋው ያጋጠመው

በቶሮንቶ ያለው የአየር ሁኔታ ከሰሞኑ በርካታ በረራዎች እንዲጓተቱ ማድረጉ ተገልጿል
በካናዳ የመንገደኞች አውሮፕላን ሲያርፍ ተገልብጦ 18 ሰዎች መቁሰላቸው ተነገረ።
74 መንገደኞችና አራት የበረራ ቡድን አባላትን አሳፍሮ ከአሜሪካ ሚኒያፖሊስ ወደ ካናዳዋ ቶሮንቶ ሲበር የነበረው የዴልታ አየርመንገድ አውሮፕላን በቶሮንቶ ፒርሰን ኤርፖርት ሲያርፍ ነው የተገለበጠው።
በማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቁ ምስሎች መንገደኞች መረገጫው ጣሪያ ከሆነው አውሮፕላን ውስጥ ለመውጣት ሲሯሯጡ አሳይተዋል።
አውሮፕላኑ ጣሪያው ወደ ምድር ቢገለበጥም አንድም መንገደኛ ህይወቱ ባለማለፉ "ደስተኛ ነን" ብለዋል የቶሮንቶ ፒርሰን ኤርፖርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዲቦራህ ፍሊንት።
ሁሉም ጉዳት የደረሰባቸው መንገደኞች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውና አንድ ህጻን እና ሁለት ጎልማሳ መንገደኞች ከባድ ጉዳት እንዳጋጠማቸውም ነው የተናገሩት።
ከመንገደኞቹ ውስጥ 22ቱ ካናዳውያን ሲሆኑ ቀሪዎቹ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች መሆናቸውን በመጥቀስም የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ላሳዩት ርብርብ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የፌደራል አቪየሽን አስተዳደር የተገለበጠው የዴልታ አየርመንገድ አውሮፕላን አጋሩ በሆነው ኢንዲቨር ኤር የሚተዳደር መሆኑን አስታውቋል።
የቶሮንቶ ፒርሰን ኤርፖርት በአደጋው ምክንያት ለጥቂት ስአት ዝግ ሆኖ ከቆየ በኋላ ዳግም አገልግሎት መጀመሩ የተነገረ ሲሆን፥ የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት ምርመራ መጀመሩ ተገልጿል።
አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚገኙ ሁለት ማኮብኮቢያዎች ዝግ ሆነው ምርመራው እንደሚካሄድም ነው የካናዳ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ ይፋ ያደርገው።
የአውሮፕላን ማረፊያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ትናንት ምሽት በሰጡት መግለጫ "ማኮብኮቢያዎቹ ደረቅ ነበሩ፤ ከባድ ነፋስም አልነበረም" ቢሉም አስቀድመው የወጡ ዘገባዎች ግን በአውሮፕላን ማረፊያው የበረዶ ብናኝ እየወረደ እንደነበር አመላክተዋል።
በስአት 64ኪሎሜትር የሚጓዝ ከባድ ነፋስ መከሰቱም ለአደጋው መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ ተገምቷል።
በቶሮንቶ ፒርሰን ኤርፖርት ባለፉት ቀናት በአየር ሁኔታ ምክንያት በርካታ በረራዎች መጓተታቸውን ነው ሲቢኤስ የዘገበው።